ጃፓናዊው ሙዚቀኛ በትዳሩ ላይ ማግጧል በሚል ከስራው ታገደ

ስመ ጥሩው ጃፓናዉ ሙዚቀኛ በትዳሩ ላይ ወስልቷል መባሉን ማመኑን ተከትሎ የወከለው ኤጀንሲ ከስራው አግዶታል።

ጆኒ ኤንድ አሶሺየትስ የተባለው ድርጅት እንዳሳወቀው ሙዚቀኛው ማሺኮ ኮንዶ "ሃሳብ የለሽ ባህርይ ጠበቅ ያለ ቅጣት ያስፈልገዋል" በማለት ገልጿል።

የ56 አመቱ ሙዚቀኛም ከስራ ጋር በተገናኘ የሚያደርጋቸው ተግባራት በሙሉ እንዲቋረጡ ሆነዋል።

በጃፓን በትዳራቸው ወስልተዋል የሚባሉ ታዋቂ ሰዎች መረር ያለ ውግዘትና ጠበቅ ያለ ቅጣት ማስተናገድ የተለመደ ነው።

ከዚህም ጋር ተያይዞ አንዳንዶች በሙያቸው የሚያስከትለውን ተፅእኖ ይተቹታል።

የሙዚቀኛው ከትዳሩ ውጭ ግንኙነት ይፋ የሆነው ባለፈው ሳምንት በአንድ አሉባልታዎችን በሚዘግብ መፅሄት ላይ ነው።

በጃፓን ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠውና በርካታ የጥበብ ሰዎችንም በመወከል የሚታወቀው ጆኒ ኤንድ አሶሺየትስ እንዳለው በትዳር ላይ ያለው ሙዚቀኛው ባህርይ ያልተገባና " ኃላፊነት የጎደለው" በሚል ተችቶታል።

"ግራ ቀኙን ካየን በኋላ በሙዚቀኛው ላይ የማያዳግም ቅጣት መጣል እንዳለብን አምነናል" ብሏል ድርቱ ያወጣው መግለጫ

በጃፓን ውስጥ በተለይም በ1980ዎቱ በጄ ፖፕ የሙዚቃ ስልት ስሙን መትከል የቻለው ሙዚቀኛው በድርጊቱ ይቅርታን የጠየቀ ሲሆን ከሙያውም ገሸሽ ብሎ ባህርይውን እንደሚገመግምና "የተሻለ ሰው ለመሆን" እንደሚጥርም ኤጀንሲው ሙዚቀኛውን ዋቢ አድርጎ በመግለጫው አካቷል።

በቅፅል ስሙ ማቺ ተብሎ የሚታወቀው ማሺኮ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ውግዘት ደርሶበታል።

በርካቶች ባህርይውን "ፀያፍ" ሲሉ የነቀፉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ለባለቤቱ ያላቸውን ኃዘኔታ ገልፀዋል።

ሆኖም ዜናው ብዙዎችን አላስደነገጠም ከዚህ ቀደምም እንዲህ አይነት ተመሳሳይ ሪፖርቶች ይወጡም ነበር ተብሏል።

አንዳንዶች የሙዚቀኛው የግል ህይወቱ ውስጥ በዚህ መንገድ ጣልቃ መገባቱን ጥያቄ አንስተዋል።

በቶክዮ የሚገኘው የሶፊያ ዩኒቨርስቲ የማህበረሰብ ጥናት ፕሮፌሰር ጄምስ ፋሬር በበኩላቸው እንዲህ አይነት ኤጀንሲዎች የታዋቂ ሰዎችን የወሲብ ህይወት በመቆጣጠር የቀደመ ታሪክ አላቸው ብለዋል።

ይህ ሁኔታ በምስራቅ እስያም ሆነ በጃፓን የተለመደ ሲሆን ወሲብን ከትዳር ውጪ መፈፀም የህዝቡን የሞራል እሴት የሚሸረሽርም ነው ተብሎ ይታመናል።

ፕሮፌሰሩ እንደሚሉትም ጥፋት ተብሎ የሚታመነው ከትዳር ውጪ መሄዱ ይፋ መሆኑ ነው እንጂ ተግባሩ በራሱ አይደለም። "ይህ አስተሳሳብ ኋላ የቀረ ነው ምክንያቱም በርካታ ወጣቶች ወሲባዊ ጉዳዮች የግል ናቸው ብለው ያምናሉ።" ብለዋል።

የሰራተኞችን የግል ወሲባዊ ባህርይ መቆጣጠር በጃፓን ስር የሰደደ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን ድርጅቶች ይህንን ሲያከናውኑ ከተገኙ እንደ ወሲባዊ ትንኮሳ እንደሚወሰድም ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ።

ሆኖም በርካታ ታዋቂ ግለሰቦች በደረሰባቸው ጫና ከስራቸው ለቀዋል።