ኮሮናቫይረስ ፡ በቻይና የኮቪድ-19 ወረርሽኝን የዘገበችው ጋዜጠኛ እሥራት ይጠብቃታል ተባለ

በቻይናዋ ዉሃን ከተማ የተከሰከሰውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን የዘገበቸው ቻይናዊት ጋዜጠኛ አምስት ዓመት እሥር እንደሚጠብቃት አዲስ የወጣ መረጃ አመለከተ።

የቀድሞ ጠበቃ የሆነችው የ37 ዓመቷ ዣንግ ዣን ባለፈው ግንቦት ነው ለእሥት የበቃችው።

ዣንግ 'ጠብ በመቀስቀስና በማነሳሳት' ወንጀል ነው የተከሰሰችው። ይህ ክስ ብዙ ጊዜ የመብት ተሟጋቾች ላይ ሲመዘዝ ይታያል።

ዣንግ ወደ ዉሃን ከተማ በማቅናት ስለ ቫይረሱ የዘገበች ብቸኛዋ ቻይናዊት ጋዜጠኛ አይደለችም።

ነገር ግን ከባለፈው የካቲት ጀምሮ ቢያንስ ሦስት ጋዜጠኞች ጠፍተዋል። ሊ ዜሁዋ የተባለ ጋዜጠኛ ሚያዚያ ላይ 'ራሴን አግልዬ ነበር' በማለት ከጠፋበት ብቅ ብሏል።

ቼን ክዊሺ የተባለው ጋዜጠኛ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር እንዳለ ሲታወቅ የሦስተኛው ጋዜጠኛ ፋንግ ቢን የት አንዳለ አድራሻው አይታወቅም።

የቻይና ባለሥልጣናት የመብት ተሟጋች ነን የሚሉ ሰዎች ላይ ጫና በማሳደር ይታወቃሉ።

በጋዜጠኛዋ ላይ የቀረበውን ክስ የሚያሳየው አንድ መዝገብ እንደሚያመለክተው፤ ዣንግ የካቲት ላይ ስለቫይረሱ ለመዘገብ ወደ ዉሃን እንዳቀናች ይተቅሳል።

የቻይና ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ጋዜጠኛዋ በወቅቱ በመንግሥት ታግተው ስለነበሩ ጋዜጠኞችም ጭምር ዘግባ ነበር ይላል።

ነገር ግን ባለፈው ዓመት ግንቦት አጋማሽ ላይ ውሃን ውስጥ ሳለች አድራሻዋ ጠፋ። በነጋታው ግን 640 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሻንግሃይ ባለሥልጣናት ቁጥጥር ሥር እንዳለች ታውቋል ይላል ቡድኑ።

ጋዜጠኛዋ ክስ የተመሠረተባት ሰኔ ላይ ነው። ከክሱ መመሥረት 3 ወራት በኋላ መስከረም ላይ ጠበቃዋ እንዲያገኛት ፈቃድ ተሰጠው።

የመብት ተሟጋች ቡድኑ ጋዜጠኛዋ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መሆኗን በመቃወም የረሃብ አድማ መትታ እንደነበር አሳውቋል።

ባፈለው አርብ ጠበቃዋ፤ ደንበኛው በይፋ እንደተከሰሰች የሚጠቁም ስልክ እንደተደወለለት ታውቋል።

የክስ መዝገቧ እንደሚያሳየው ጋዜጠኛዋ ሐሰተኛ መረጃ 'በፅሁፍ፣ በተንቀሳቃሽ ምስልና በሌሎች መንገዶችና ማኅበራዊ ድር አምባዎች አስተላልፋለች' ይላል።

አልፎም ከውጭ አገራት መገናኛ ብዙሃን ጋር ቃለ ምልልስ አድርጋለች ሲል የክስ መዝገቧ ያትታል።

ጋዜጠኛዋ ከአራት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እሥር ልትቀጣ እንደምትችል መዝገቡ ይናገራል።

ጋዜጠኛዋ ከዚህ በፊትም ሆንግ ኮንግ ውስጥ ያሉ የመብት ተሟጋቾችን በመደገፏ ምክንያት ቃሏን ለመርማሪዎች እንድትሰጥ ተደርጋ ነበር።