ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጉግል በጂሜይል አድራሻቸው ፎቶ ለሚያስቀምጡ ማስከፈል ሊጀምር ነው
ጉግል በጂሜይል ዲጂታል ፖስታ ሰንዱቃቸው ውስጥ ብዙ ፎቶ የሚያስቀምጡ ደንበኞቹን ገንዘብ ማስከፈል ሊጀምር ነው።
ጂሜይል የተሰኘ የኢሜል አገልግሎት የሚሰጠው ጉግል ደንበኞቹን ክፍያ የሚጠይቀው ከተወሰነ መጠን በላይ ለሚመዝኑ ፎቶዎች ብቻ ነው።
ይህ የሆነው እንደ ጂሜይል ሁሉ በጉግል ኩባንያ ከሚሰጡ የጉግል አገልግሎቶች አንዱ የሆነው "ጉግል ፎቶ" የመጋዘን ኪራይ ክፍያ ደንበኞቹን ማስከፈል እንዲጀምር በመደረጉ ነው። ይህ "የጉግል ፎቶ" የዲጂታል መጋዘን ገደብ ደግሞ በተዘዋዋሪ በጂሜይል የሚቀመጡ ፎቶዎችን ብዛት እንዲወስን አድርጓል።
"ጉጉል ፎቶ" ለደንበኞቹ ገደብ የለሽ የፎቶ ማጠራቀም ዲጂታል መጋዘን አገልግሎት ሲያቀርብ ነበር።
ይህ የድርጅቱ የፎቶ ማጠራቀሚያ አገልግሎት የተጀመረው በ2015 እንደ አውሮፓዊያኑ ነበር።
ያን ጊዜ ጉግል "ደንበኞች ስለ ፎቶ መጠን ሳይጨነቁ እንደልባቸው በኔ ዲጂታል መጋዘን ውስጥ ማጠራቀም ይችላሉ" ሲል ብሥራትን አስነግሮ ነበር።
አሁን ላይ ይህን ነጻ አገልግሎት ለምን ለማቆም እንደወሰነ የተጠየቀው ጉግል "አገልግሎቱን ገደብኩ እንጂ አላቆምኩም፤ ደንበኞቼ አሁንም እስከ 15 ጂቢ የሚመዝን የፎቶ ክምችት በነጻ በዲጂታል መጋዘኔ ውስጥ ማስቀመጥ ይችላሉ ብሏል።
ይህ የ"ጉግል ፎቶ" የሚዛን ምጣኔ በጉግል ድራይቭና በጂሜይል የዲጂታል ደብዳቤ ውስጥ መቀመጥ የሚችለውን ነጻ የፎቶ ክምችት መጠንን ይጨምራል። በመሆኑም ሰዎች ከዚህ ቀደም ያለ ገደብ በጂሜይላቸው የሚያስቀምጡት ፎቶ ብዛትም በተዘዋዋሪ ይወሰናል ማለት ነው።
ከ15 ጊጋ ባይት በላይ መጠን ያለው ፎቶ ለማጠራቀም ከዚህ በኋላ ጉግል ክፍያን ይጠይቃል።
በዚህ የ15 ጊጋ ባይት ገደብ ውስጥ ከሰኔ 2021 በፊት የተቀመጡ ፎቶዎች አይደመሩም።
በዚህ የጉግል ውሳኔ የተቀየሙ ደንበኞች በማኅበራዊ ሚዲያ ቅሬታቸውን ሲገልጡ ከርመዋል።
ገደብ የለሽ አገልግሎት በሚል ማስታወቂያ አታሎ ደንበኛ ካደረጋቸው በኋላ ሐሳቡን መቀየሩ ጉግል ለደንበኞቹ ምን ያህል ታማኝ እንዳልሆነ ያሳያል ያሉም ነበሩ።
"ጉግል ፎቶ" የተሰኘው አገልግሎት በፈረንጆቹ 2015 ሲጀመር ኩባንያው "የሕይወት ዘመን ትዝታዎን ያለገደብ አስቀምጡ ስንል የምራችንን ነው!" እያለ ማስታወቂያ ሲያስነግር ነበር።
በ "ጉግል ፎቶ" ከፎቶ ባሻገር ቪዲዮዎችን ለማጠራቀምም አገልግሎቱ ክፍት ነበር።
ጉግል እንደሚለው እስከአሁን ከደንበኞቹ 4 ትሪሊዮን የሚሆኑ ፎቶዎች "ጉግል ፎቶ" ማጠራቀሚያ ውስጥ መቀመጣቸውን 28 ቢሊዮን ፎቶዎች እና ቪዲዯዎች ደግሞ በየሳምንቱ ወደ መጋዘኑ እንደሚጋዙ አስታውቋል።
ጉግል በተጨማሪ በሦስቱ ተመጋጋቢ አገልግሎቶቹ ማለትም በጉግል ፎቶ፣ በጉግል ድራይቭ እና በጂሜይል በድምሩ 4 ሚሊዮን ጊጋባይት የሚመዝኑ ፎቶዎች በቀን በቀን ይቀመጣሉ።
"ጉግል ፎቶ"ን ያለገደብ በማስቀመጥ አማራጭ ተጠቅሞ ገበያውን መቆጣጠር ችሎ ቆይቷል። ፒክስል ስልኮቹን ተመራጭ እንዲሆኑ ያደረጋቸውም ይኸው ተጨማሪ ነጻ አገልግሎቱ ነበር።
ጉግል አሁን እንደሚለው 15 ጊጋ ባይት የሚሆነው ነጻ አቅርቦት ለአብዛኛዎቹ ደንበኞቹ ከበቂ በላይ ሲሆን 80 ከመቶ የሚሆኑ ደንበኞቹንም በርካታ ዓመታትን ሳይጨነቁ የሚያገለግላቸው የዲጂታል መጋዘን ስፋት ነው።
ይህ 15 ጊጋ ባይት ጂሜይልን ጨምሮ በድራይቭና በጉግል ፎቶ አገልግሎትች የሚገኙ ፎቶዎችን ይጨምራል።
"80 ከመቶ ተጠቃሚዎቼ ለሦስት ዓመታት ምንም ሳያስቡ ነጻ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉ፣ ምክንያቱም የሚያስቀምጡት ፎቶ ብዛት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም" ብሏል ኩባንያው።
ከ15 ጊጋ ባይት በላይ ማስቀመጥ የሚፈልጉ ደንበኞች 8 ፓውንድ ክፍያ በየወሩ ሊጠየቁ ይችላሉ፣ ይህም 2ሺህ ጊጋ ባይት ወይም 2 ቴራ ባይት ማስቀመጫ ዲጂታል መጋዘን ባለቤት ያደርጋቸዋል ማለት ነው።