የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ሴቶችን መግደል ከባድ ወንጀል እንዲሆን ልታደርግ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ሴት ልጅ ቤተሰብ አዋረደች በሚል ከወግ፣ ሃይማኖትና ባሕል ያፈነገጡ ተግባራትን ፈጽማለች ተብሎ ሲታሰብ የሞት ቅጣት በገዛ ቤተተሰቦቿ ሊፈጸምባት ይችላል፡፡
በዚህ ረገድ በገዳዮቹ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ልል ሆኖ ቆይቷል፡፡አሁን ግን የተባበሩት ኤምሬትስ የሕግ ማሸሻያ ለማድረግ ዝታለች፡፡
ማሻሻያው ሴቶችን በገደሉ የቤተሰብ አባላት ላይ ዳኞች አነስተኛ ቅጣት ወይም የቅጣት ማቅለያ እንዳያደርጉ የሚያስችል ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹ ወንጀሎች ‹‹የክብር ግድያ›› ወይም ‹‹ኦነር ኪሊንግ› በሚል ተቀጽላ እንደ ትክክለኛ እርምጃ የመውሰድ አዝማሚያዎች ነበሩ፡፡
አሁን ይህ እንዲቀር ይደረጋል ተብሏል፡፡ሰውን ገድሎ የክብር ግድያ ብሎ ነገር የለም የሚሉ የመብት ታጋዮችም መጠርያው ሊቀየር ይገባል ይላሉ፡፡
የኤምሬትስ ባለሥልጣናት በበኩላቸው የቤተሰብን ክብር ለማስጠበቅ በሚል በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች እንደ ማንኛውም ግድያ ወንጀል እንዲታዩ ለማድረግ ቆርጦ ተነስቷል፡፡
የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች እንደሚሉት በመላው ዓለም ሴት ልጅን ለቤተሰብ ክብር ማስጠበቂያ በሚል መግደል እጅግ እየተዘወተረ ነው፡፡ በየዓመቱም በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች በዚህ መልኩ ይገደላሉ፡፡
ቤተሰብ አዋረደች በሚል በሴቶች ላይ የሚደረጉ ግድያዎች እንደ ሌሎች ግድያዎች ለማየት የኤምሬትስ መንግሥት መወሰኑ ትልቅ እርምጃ ነው በሚል እየተወደሰ ነው፡፡









