ተመራጩ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን 'አሜሪካን አንድ ለማድረግ' ቃል እገባለሁ ብለዋል

ጆ ባይደን 'አሁን ጊዜው አሜሪካ የምናክምበት' ነው ሲሉ ከተመረጡ በኋላ ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግር ላይ ተደምጠዋል።

ባይደን 'አሜሪካን ለመከፋፈል ሳይሆን አንድ ለማድረግ' ቃል እገባለሁ ብለዋል።

ዴልዌር በተሰኘው ግዛት ንግግር ያደረጉት ባይደን ላልመረጧቸው ሰዎች 'እስቲ ዕድል እንሰጣጥ' ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ጆ ባይደን ተቀማጩን ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ታሪክ ከፍተኛ የሆነ ድምፅ አምጥተው ነው የረቷቸው።

ዶናልድ ትራምፕ እስካሁን የምርጫውን ውጤት አልተቀበሉም፤ ይፋ ንግግርም አላደረጉም።

የጆ ባይደን አሸናፊነት ሲታወጅ ፕሬዝደንት ትራምፕ ጎልፍ እየተጫወቱ ነበር።

ትራምፕ ከ1990ዎቹ በኋላ አንድ ጊዜ ብቻ መርተው ከሥልጣን የወረዱ ፕሬዝደንት ይሆናሉ።

ተቀማጩ ፕሬዝደንት ምርጫው ተጨበርብሯል የሚል ያልተረጋገጠ ፅንሰ ሃሳብ በማንሳት እከሰላሁ ብለዋል።

ጆ ባይደን አሸናፊነታቸው እንደታወጀ በአሜሪካ ትላልው ከተሞች ነዋሪዎች ለደስታ ወደ አደባባይ ተመዋል።

የትራምፕ ደጋፊዎች ደግሞ የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል። የደረሰ ጉዳት ግን የለም ተብሏል።

ዴልዌር በምትገኘውና ባደጉባት ዊልሚንግተን ከተማ ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቻቸው ንግግር ያሰሙት ባይደን ከምንም በላይ አሜሪካውያንን አንድ ለማድረግ ቆርጠው እንደሚሠሩ አስረግጠዋል።

እስካሁን ድረስ በተሰበሰበው ድምፅ የ74 ሚሊየን አሜሪካውያንን ድምፅ ያገኙት ተመራጩ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አፍሪካዊ አሜሪካውያንን መራጮችን አመሰግነዋል።

አልፎም ለትራምፕ ድምፃቸውን ለሰጡ መራጮች መልዕክት እንካቹ ብለዋል።

"አሁን ጊዜው ከፋፋይ የሆኑ ንግግሮችን ትቶ፤ ግለት ቀንሶ እርስ በርስ የመተያያና የመደማመጫ ጊዜ ነው" ብለዋል።

የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አጥልቀው ወደ መድረክ የወጡት ባይደን በቅርቡ የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ የሚከታተል ኮሚቲ አቋቁመው ሲመተ ሹመታቸው በተከናወነ ማግስት ወደሥራ እንደሚገቡ ቃል ገብተዋል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የወሰዱት እርምጃ እምብዛም አይደለም ተብለው ይተቻሉ።

አሜሪካ በኮሮናቫይረስ ምክንያት 237 ሺህ ሰዎች አጥታለች፤ ይህም ከዓለም ትልቁ ቁጥር ነው።

ምክትሏ ከማላ

የተመራጩ ፕሬዝደንት ምክትል ሆነው የመተረጡት ከማላ ሃሪስ በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ምክትል ፕሬዝደንት በመሆን ታሪክ ይሠራሉ።

አልፎም የመጀመሪያዋ ጥቁርና እስያዊ አሜሪካዊ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው ነው በሚቀጥለው ጥር የሚሾሙት።

"እኔ የመጀመሪያዋ ልሁን እንጂ የመጨረሻዋ ግን ፈፅሞ አልሆንም" ሲሉ አነቃቂ ንግግር አሰምተዋል።

"ተስፋ፣ አንድነት፣ ትህትና፣ ሳይንስ እንዲሁም እውነትን መርጣችኋል - ጆ ባይደን ቀጣዩ ፕሬዝደንት እንዲሆኑ ድምፅ ሰጥታችኋል። ከፊት ለፊታችን ያለው መንገድ አልጋ በአልጋ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን አሜሪካ ዝግጁ ናት። እኔና ጆም እንዲሁ።"

ጆ ባይደንና ከማላ ሃሪስ በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት 2021 የመጀመሪያ ወር በኦፊሴላዊ በዓለ ሲመት ሥልጣን ይረከባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ነገር ግን እስካሁን ሽንፈታቸውን በፀጋ ያልተቀበሉት ፕሬዝደንት ትራምፕ ቀጣይ ምን ይሉ ይሆን የሚለው አልታወቀም።