ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኬንያው የገበያ ማዕከል የሽብር ጥቃት ሁለት ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ
በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ የሚገኘው ዌስት ጌት የገበያ ማዕከል ላይ ጥቃት ፈፅመዋል በሚል በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ከነበሩት መካከል ሁለቱ በ18ና 33 አመት እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።
እስር የተበየነባቸው ግለሰቦች መሃመድ አህመድ አብዲና ሁሴን ሃሰን ሙስጠፋ ሲሆኑ የሽብር ተግባሩን በማቀነባበር እንዲሁም ለጥቃት አድራሾቹ ድጋፍ ሰጥተዋል በሚል ክስ ነው።
በአልሻባብ ደረሰ በተባለው በዚህ ጥቃት ቢያንስ 67 ሰዎች ሞተዋል ተብሏል። ጥቃቱ የደረሰው በጎሮጎሳውያኑ 2013 ነው።
የሽብር ጥቃቱን በዋነኝነት የፈፀሙት አራቱ ታጣቂዎች በመገበያያ ማዕከሉ ፍርስራሽ ተገድለው እንደተገኙ የኬንያ መንግሥት አሳውቋል።
በዌስት ጌት የመገበያያ ማእከል በደረሰው ጥቃት ታጣቂዎች በሸማቾች ላይ ተኩስ የከፈቱ ሲሆን፤ ለአራት ቀናት ያህልም ቆይቷል።
በዚህም ቢያንስ 62 ንፁሃን ዜጎች፣አምስት ፖሊሶችና አራት ታጣቂዎች ተገድለዋል።
በሽብር ጥቃቱ ተጠርጥሮ የነበረው ሌላኛው ግለሰብ ፍርድ ቤት በነፃ ቢያሰናብተውም ባልታወቁ ታጣቂዎች መታገቱ ተሰምቷል።
ሊባን አብዱላሂ ኦማር የተባለው ግለሰብ በዚህ ሽብር ጥቃት እጁ የለበትም ብሎ ፍርድ ቤቱ ከሶስት ሳምንታት በፊት በነፃ ቢያሰናብተውም ያለበት አይታወቅም።
ወንድሙ የሽብር ጥቃቱን ካደረሱት መካከል አንዱ ነው የተባለ ሲሆን በወቅቱም በፖሊስ ተገድሏል።
የሶማሌ ስደተኛ የሆነው ሊባን የታገተውም ከፖሊስ ፀረ-ሽብር ቢሮ ሲወጣ መሆኑንም የእስልምና እምነት ተከታዮች የሰብዓዊ መብት ላይ የሚሰራ መንግሥታዊ ድርጅት ዳይሬክተር ኬሌፍ ካሊፋ ለቢቢሲ አሳውቀዋል፥
ታስሮበት ከነበረው ካማቲ እስር ቤትም ከተለቀቀ በኋላም ፀረ-ሽብር ቢሮው የሄደው መጨረስ ያለበትን ጉዳዮችም ለማጠናቀቅ ነው ተብሏል።
ያገቱት ግለሰቦችን ማንነት በተመለከተ ማንም አስተያየት ከመስጠት ቢቆጠብም በጠራራ ፀሃይና በቀን እንዲህ ታጥቀው ሊባንን ሊያግቱት የሚችሉት ከፖሊስ ፀረ-ሽብር ቢሮ ጋር ግንኙነት ያላቸው እንደሆኑ በርካቶች እየተናገሩ ነው።
በሽብር ተጠርጥረው ፍርድ ቤት በነፃ ያሰናበታቸው ግለሰቦች አብዛኛውን ጊዜ ደብዛቸው ይጠፋል ወይም ተገድለው ይገኛሉ። በግድያቸውም ሆነ በመጥፋታቸው ተጠያቂ የሚሆን አካልም የለም።
ሶማሊያ መሰረቴ ነው የሚለው አልሸባብ በርካታ ጥቃቶችን በኬንያ አድርሷል።
ኬንያ ሽብርተኝነትን እዋጋለሁ በሚል ወታደሮቿን በሶማሊያ አሰማርታለች።