ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትምህርት፡ በሰላም መደፍረስ ምክንያት ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎች እጣ ፈንታ ምን ይሆናል?
በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት አቋርጠው የነበሩ ዩኒቨርስቲዎች በጥቅምት ወር መጨረሻ ሳምንት አንስቶ ተመራቂ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር ለቢቢሲ ተናገረ።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ከጥቅምት 23 እስከ 30/2013 ዓ. ም የመጀመሪያ ዙር የተማሪዎች ቅበላ እንደሚያርጉ ተገልጿል።
የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ደቻሳ ጉርሙ ለቢቢሲ እንዳስረዱት ከጥቅምት ወር አንስቶ የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎች ጥሪ ይከናወናል።
ተማሪዎቹ ቀርተዋቸው የነበሩ ኮርሶች በቀጣይዎቹ ሁለት ወራት ውስጥ እንዲያጠናቅቁ መወሰኑን የተናገሩት አቶ ደቻሳ፤ ከዚያ በኋላ ደግሞ የኮሮናቫይረስ ሁኔታን በማየት ለተቀሩት ተማሪዎች ጥሪ ይተላለፋል ብለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኮቪድ-19ን እየተከላከሉ ትምህርትና ስልጠናን ለማስቀጠል ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ከጥቅምት 23-30/2013 ዓ. ም አስፈላጊውን ዝግጅት በማጠናቀቅ የመጀመሪያ ዙር የተማሪዎች ቅበላ እንዲያደርጉ ማሳሰቡ ተዘግቦ ነበር።
በቅርቡ ዩኒቨርስቲዎች በሃዋሳ ከተማ ለሶስት ቀናት ባካሄዱት ስብሰባ ትምህርት ለማስጀመር መወሰናቸውን አቶ ደቻሳ ጨምረው ተናግረዋል።
በአገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ ላለፉት ሰባት ወራት ትምህርት ለማቋረጥ መገደዳቸው ይታወሳል።
በጉዳዩ ላይ ቢቢሲ ካነጋገራቸው ዩኒቨርስቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የወለጋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሐሰን የሱፍ ከጥቅምት 23 እስከ 30 2013 ዓ. ም ባሉት ቀናት ውስጥ የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎችን እንቀበላለን ብለዋል።
"በቀጣይ ደግሞ የሁለተኛ ዓመት እና ከዚያ በላይ ያሉትን ተማሪዎች ጥሪ እናደርጋለን" ሲሉ የሌሎች ተማሪዎችን እጣ ፈንታ ያስረዳሉ።
ከሁለተኛ ዓመት እና ከዚያ በላይ ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች የአንደኛ መንፈቀ ዓመት ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ለሁለተኛ መንፈቀ ዓመት ዝግጅት ላይ በነበሩበት ወቅት በኮሮናቫይረስ ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ቤተሰባቸው መመለሳቸውን ዶ/ር ሐሰን ያስታውሳሉ።
የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች ግን የአንደኛ መንፈቀ ዓመት ፈተናቸውን ጀምረው ሳያጠናቅቁ መሄዳቸውን ተናግረው፤ መማር የሚገባቸውን ቁልፍ የሆኑ ትምህርቶች በመለየት በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ አስተምሮ ለማስጨረስ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን አብራርተዋል።
ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የሀሮማያ እና መደወላቡ ዩኒቨርስቲዎችም የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረው፤ በተመሳሳይ የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በሰላም መደፍረስ ምክንያት ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎችስ?
ባለፈው ዓመት የትምህርት ዘመን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በፊት በአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች ተከስቶ የነበረውን የሰላም መደፍረስ ተከትሎ አንዳንድ ተማሪዎች ትምህርታቸው አቋርጠው ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለሳቸው ይታወሳል።
ለምሳሌ ከኦሮሚያ ክልል የሄዱና በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ፣ በተመሳሳይም ከአማራ ክልል የሄዱና በኦሮሚያ ክልል ሲማሩ የነበሩ ተማሪዎች ባጋጠመው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ቤተሰቦቻቸው ተመልሰዋል።
ይሁን እንጂ አንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች ባደረጉት ውይይት ተማሪዎች ተመልሰው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ተደርጎ እንደነበር ይናገራሉ።
ከእነዚህም መካከል የወለጋ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ሐሰን የሱፍ እንዳሉት፤ በዩኒቨርስቲው አልፎ አልፎ ተከስቶ በነበረው የሰላም መደፍረስ ትምህርታቸውን በማቋረጥ ወደ ቤተሰቦቻቸው ተመልሰው የነበሩ ተማሪዎች ተመልሰው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ መተላለፉን ያስታውሳሉ።
በዚሁ መሰረት ገሚሶቹ ተመልሰው የነበረ ቢሆንም ገሚሶቹ ደግሞ በነበረው ሁኔታ ስጋት ገብቷቸው ሳይመለሱ መቅረታቸውን ተናግረዋል።
"እነዚህ ተማሪዎች ተመልሰው እኛ ጋር እንዲማሩ እንፈልጋለን፤ ይሁን እንጂ የአንደኛ ሴሚስተር ትምህርት ስላመለጣቸው፣ ፈተናም ስላልተፈተኑ ከመጀመሪያው መጀመር የግድ ይላቸዋል"
ከዚህም በተጨማሪንእነዚህ ተማሪዎች ትምህርት ሲያቋርጡ መሙላት የሚገባቸውን ቅጽ (ዊዝድሮዋል) ሳይሞሉ ግቢውን ለቅቀው መውጣታቸውን የሚናገሩት ዶ/ር ሐሰን፤ አሁን ምን ዓይነት ውሳኔ ነው የሚተላለፈው በሚለው ላይ ትምህርት ሚኒስቴር እስካሁን ድረስ ያለው ነገር እንደሌለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል በሰላም መደፍረስ ትምህርት ተቋርጦቸባቸው ከነበሩት ዩኒቨርስቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የመደወላቡ ዩኒቨርስቲ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ፈለቀ ረጋሳ በበኩላቸው፤ በዘንድሮው ዓመት የሚመረቁ 2016 ለሚሆኑ ተማሪዎች ጥሪ መተላለፉን ገልፀው ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ ይናገራሉ።
በሌላ በኩል አምና ገጥሞ በነበረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠው የሄዱ ተማሪዎች መኖራቸውን ያስታወሱት ዶ/ር ፈለቀ፤ " ይሁን እንጂ በኋላ ላይ ባደረግነው ጥሪ 75 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ተመልሰው ትምህርታቸውን መከታተል ችለዋል" ብለዋል።
በወቅቱ አምልጧቸው የነበረውን ትምህርት ለማካካስም አስተማሪዎች በተጨማሪ ሰዓት ሲያስተምሯቸው እንደነበር ይናገራሉ።
"ጥሪ ቢተላለፍም 25 በመቶ የሚሆኑት ሳይመለሱ ቀርተዋል። የሚተላለፈው ውሳኔም ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዩኒቨርስቲው ተማሪዎች በሚሆን ሁኔታ በዩኒቨርስቲው ሴኔት የሚወሰን ይሆናል፤ ለእነርሱ ብቻ የሚሰራ ሕግ አይኖርም።"
ዶ/ር ፈለቀ እንደሚሉት በሕጉ መሰረት የሚታገዱ ከሆነ ይታገዳሉ የሚመለሱ ከሆነም ተመልሰው ትምህርታቸውን ይከታተላሉ።
በተመሳሳይም የሃሮማያ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጀማል የሱፍ ባለፈው ዓመት በነበረው የሰላም መደፍረስ ትምህርታቸውን አቋርጠው የሄዱ ተማሪዎችን በሚመለከት እስካሁን የተላላፈ አዲስ ውሳኔ እንደሌለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በሰላም መደፍረስ ምክንያት ወደቤተሰቦቻቸው የተመለሱ ተማሪዎችን በሚመለከት እንደ አገር በትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ መተላለፍ እንዳለበት ዶ/ር ጀማል ይናገራሉ።
ይህንኑ ጉዳይ በሚመለከት ቢቢሲ ጥያቄ ያቀረበላቸው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነት አቶ ደቻሳ ጉርሙ፤ እስካሁን በዚህ ጉዳይ ላይ የተላለፈ ምንም ዓይነት ውሳኔ አለመኖሩን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
የተማሪዎቹ ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ከዩኒቨርስቲዎቹ ከተጣራ በኋላ እንዴት ይህን ችግር እንፍታ በሚለው ላይ እየተሰራ እንደሆነ በመግለጽ "ውሳኔ ላይ ስንደርስ የምናስታውቅ ይሆናል" ብለዋል።
"ያለን አንድ አገር ስለለሆነ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላ ክልል አልሄድም የሚል አስተሳሰብ ካለ አናስተናግድም" ሲሉም ሃሳባቸውን ይቋጫሉ።