45 ዓመታትን በሰማይ ላይ

ለ45 ዓመታት ያበረሩት ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ፓይለት፤ ካፒቴን ተስፋይ አምባዬ።

ካፒቴን ተስፋይ አየር መንገድ የበረራ መምሪያ ኃላፊ በመሆን ለአምስት ዓመታት አገልግለዋል።

ካፒቴን ተስፋይ ወላጅ አባታቸው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በጁሩንድ (ገንዘብ ሚኒስቴር) ውስጥ የአገር ውስጥ ገቢ ሹም ስለነበሩ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ከቦታ ወደ ቦታ በመዘዋወር ነበር።

ማይጨው ከተማ ውስጥ የተወለዱት ካፒቴን ተስፋይ፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በተንቤንና መቀለ ተከታትለዋል።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአፄ ዮሐንስ ትምህርት ቤት ተምረዋል። የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ጥሩ ውጤት በማምጣታቸው በ1966 ዓ. ም. ወደ አዲስ አበባ አምርተው ነበር።

ወቅቱ ንጉሡ ከሥልጣናቸው ወርደው ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት የተተካበት እና ሁኔታው ያልተረጋጋ ስለነበር ከወንድማቸው ውስ ጋር ቤትጥ ቁጭ ብለው ይውሉ እንደነበር ያስታውሳሉ።

አንድ ቀን አንድ የጎረቤት ልጅ፣ ‘ፓይለት ለመሆን ስልጠና መወስድ የምትፈልጉ ተመዝገቡ’ የሚል ማስታወቂያ መለጠፉን ነገራቸው።

የያኔው ተማሪ ተስፋይ ግን ብዙም ደስተኛ አልነበሩም። ቢሆንም ግን ቁጭ ብሎ ከመዋል ለምን አልሞክርም በሚል ለመወዳደር ማመልከታቸውን ያስታውሳሉ።

በወቅቱ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የአብራሪነት ስልጠና ወስዶ ለመቀጠር ካመለከቱት 600 ያህል ወጣቶች በፈተና ተጣርተው መጨረሻ ላይ 8 ልጆች አለፉ። ከእነዚህም መካከል አንዱ ተስፋይ ነበሩ።

በዚሁ መልኩ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራቸውን አሀዱ ብለው ጀመሩ።

ካፒቴን ተስፋይ ሥራ ሲጀምሩ ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት የተረፉትን ‘ዲሲ ስሪ’ (ዳኮታ) አውሮፕላን ማብረር መጀመራቸውን ያስታውሳሉ።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ የተቀጠረ ጀማሪ አብራሪ ለአንድ ዓመት ረዳት አብራሪ በመሆን መሥራት ስለሚጠበቅበት ረዳት አብራሪ ሆነው አገልግለዋል።

ካፒቴን ተስፋይ፤ በአሁኑ ሰዓት ‘ትሪፕል ሰቨን’ (ቦይንግ 777) የሚያበሩ የድርጅቱ አንጋፋ ፓይለት ናቸው።

አውሮፕላን አየር ላይ እንዴት 'መንሳፈፍ' ቻለ?

አውሮፕላን ሰው ጭኖ እንደምን በአየር ላይ መንሳፈፍ ቻለ? በሚል ታዳጊ ልጆች መንደር ውስጥ ይከራከራሉ። አንዱ በክንፍ ታግዞ ነው የሚበረው ይላል። ሌላኛው ደግሞ በሞተር ምክንያት ነው የሚበረው ብሎ ይከራከራል።

ቀጥለው ለምን ዘበኛውን አንጠይቅም? በማለት አጠገባቸው የነበሩትን አዛውንት ጠየቁ። የተከራከሩበትን ርዕስና የየራሳቸውን ግምት በማቅረብ፤ አዛውንቱ ማንኛቸው ትክክል እንደሆኑ ፍርድ እንዲሰጧቸው በጽሞና ጠበቁ።

አጋጣሚ ሆኖ ዘበኛው ‘ሁሉንም ነገር አውቃለሁ’ ባይ ስለነበሩ፤ ሁላችሁም ተሳስታችኋል በማለት የሚከተለውን መልስ ሰጡ።

ሁለት አጋንንቶች አሉ። አንዱ የመሬት ሁለተኛው ደግሞ የሰማይ በመባል ይከፈላሉ። መሬት ላይ ያለው ጋኔን አውሮፕላንዋን አንደርድሮ ከመሬት ያስነሳትና ‘ያዝ እንግዲህ ተቀበል’ ብሎ ሰማይ ላይ ላለው ጋኔን ያስረክበዋል። ሰማይ ላይ የቆየው ጋኔን ደግሞ አውሮፕላንዋን ይዞ ይበርና ልታርፍ ስትል አንተ ደግሞ በፊናህ ተቀበል ብሎ መሬት ላይ ላለው መልሶ ይሰጠዋል።

አዛውምቱ “መልሱ ይህ ነው። በማታውቁት ነገር ጥልቅ አትበሉ” አሏቸው።

ካፒቴን ተስፋይ ይህንን ገጠመኝ አብዱል ከሚባል ጓደኛቸው የሰሙ ዕለት ፈገግ ማለታቸውን ይናገራሉ።

ዋናው የአውሮፕላኑ በአየር ላይ ያለ ችግር መንሳፈፍ ምስጢሩ ሞተርና ክንፍ ላይ የሚገኘው ‘ኤሮ ዳይናሚክ’ ነው ሲሉ ለቢቢሲ በአጭሩ መልሰዋል።

45 ዓመታት በሰማይ ላይ

ቀደም ሲል በኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንብ መሠረት አንድ ካፒቴን 60 ዓመት ሲሞላው ጡረታ ይወጣል። አሁን ላይ ወደ 65 ዓመት ከፍ እንዲል መደረጉን ካፒቴን ተስፋይ ይገልጻሉ።

በዚህ መሠረት ካፒቴኑ በያዝነው ጥቅምት ወር ውስጥ ጡረታ ይወጣሉ።

ለ45 ዓመታት ያለማቋረጥ ማብረራቸውን የሚናገሩት ካፒቴኑ፣ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ 27 ሺህ ሰዓታት በመብረር ከአንድ መቶ በላይ አገራትን አዳርሰዋል።

“ከዕድሜዬ በላይ ነው እየኖርኩ ያለሁት፤ የሌላ ሰው ዕድሜ እየኖርኩ ያለሁ ያህል ይሰማኛል። ምክንያቱም አንድ ሰው ባለው ዕድሜ ውስጥ የተወሰኑ ነገሮችን ብቻ ነው ማድረግ የሚችለው። እኔ ግን ከተወሰኑ ነገሮች በላይ በማየቴ፣ ከተፈቀደልኝ ዕድሜ በላይ የኖርኩ ሰው ነኝ ብዬ ነው የማስበው” ይላሉ ካፒቴን ተስፋይ።

አንዳንድ ጊዜ ኢትዮጵያ ከ50 ዓመታት በኋላ የምትደርስበትን የዕድገት ደረጃ በሌሎች አገራት ስላዩት፤ “አገራችን ውስጥ ያሉ ሰዎች ከማየታቸው አስቀድሞ እኔ አይቼዋለሁ” የሚል ስሜት እንደሚሰማቸው ይገልጻሉ።

ካፕቴን ተስፋይ በ45 የበረራ ዓመታት ውስጥ በጣም ብዙ ችግሮች ቢያጋጥማቸውም፤ ይህ ነው የሚባል የከፋ አደጋ አልደረሰባቸውም።

እንዲያውም ከዕድለኞቹ አንዱ ነኝ ብለው እንደሚያስቡ ይናገራሉ።

የአውሮፕላኑ አንድ ሞተር መጥፋት የተለመደ ነው

ከዕለታት አንድ ቀን ካፒቴን ተስፋይ አውሮፕላን አስነስተው ይበራሉ።

ከሰባት ደቂቃዎች በኋላ በሞተር ዘይት ውስጥ በተፈጠረ ሙቀት ምክንያት ዘይት ይጎድላል። ይህን የታዘቡት ረዳት አብራሪ ለካፒቴኑ ሪፖርት ያደርጋሉ።

ከዚያ በኋላ የማስጠንቀቂያ ቀይ ምልክት ከመብራቱ በፊት ሞተሩን አጠፉት። ከሁለቱ ሞተሮች አንዱ ከጠፋ ደግሞ በረራውን ማስቀጠል አይቻልም። ወድያውኑ አውሮፕላኑ ተመልሶ እንዲያርፍ በማድረግ የብዙዎች ሕይወት እንዲድን አድርገዋል።

“በረራ ላይ እያለህ ሞተር ከጠፋ ነገሩ ቀላል ነው። አውሮፕላኑ በማኮብኮብ ላይ ለመነሳት በሚያደርገው ቅፅበት ሞተር ከጠፋ ግን ከባድ ነው። አውሮፕላኑ አኮብኩቦ ከመነሳቱ በፊት ባለው ‘የመነሳትና የመቆየት’ ቅፅበት፣ ሞተሩ ቢጠፋም ማቆም ብሎ ነገር ከቶውኑ አይታሰብም። አውሮፕላኑ የግድ መነሳት አለበት። ከተነሳ በኋላ ግን አይቀጥልም። ዞሮ በፍጥነት ተመልሶ ማረፍ ይኖርበታል። እንደዚህ አይነቱ አጋጣሚ ግን አልፎ አልፎ የሚታይ ክስተት ነው” ሲሉ ያስረዳሉ።

በአሁኑ ጊዜ መኪና ከመንዳት በበለጠ አውሮፕላን ማብረር አተማማኝ ነው። አውሮፕላን ውስጥ ከመኪና በተሻለ “ደህንነትህ የተጠበቀ ይሆናል” ይላሉ ካፒቴን ተስፋይ።

'ብላክ ቦክስ'

አውሮፕላን የመከስከሱ ዜና ሲሰማ 'ብላክ ቦክሱ' ተገኝቷል ወይ የሚል ጥያቄ ቀድሞ አብሮ የሚነሳ ጉዳይ ነው።

ካፒቴን ተስፋይ "ሰው ከመሞቱ በፊት በኑዛዜ ወቅት ምን ብሎ ተናዞ ይሆን ብለን እንደምንጠይቅ አድርጎ ማሰብ ይቻላል። በተለይ ደግሞ ከመሞቱ ከ30 ደቂቃዎች በፊት ምን ብሎ ተናግሮ ነበር የሚለውን መረጃ የሚሰጠን ይሆናል።"

'ብላክ ቦክስ' ወይም ጥቁሩ ሳጥን እንደሱሙ ቀለሙ ጥቁር ሳይሆን ብርቱኳናማ ነው።

ብላክ ቦክስ በየሰላሳ ደቂቃው እየደመሰሰ እና እየቀዳ መረጃዎችን ይቀመጣል። አንድ አውሮፓላን ላይ አደጋ ቢያጋጥም ከአደጋው በፊት የነበሩ የመጨረሻዎቹን 30 ደቂቃ መዝግቦ ይይዛል ማለት ነው።

የብላክ ቦክሱ በድምጽ ቅጂ መያዣ ክፍሉ አብራሪዎቹ አደጋው ከመድረሱ በፊት የተነጋገሩትን ድምጽ ቀርጾ ያስቀምጣል።

ካፒቴን ተስፋይ እንደሚሉት ብላክ ቦክሱ በጣም አስፈላጊ መሳርያ ስለሆነ በአደጋ ወቅት በቀላሉ ጉዳት እንዳይደርሰበት ታስቦ በአውሮፕላኑ ጭራ አከባቢ ነው የሚቀመጠው። ምክንያቱ የአውሮፕላን የኋላ ጫፍ ክፍል ከአደጋው የመትረፍ ዕድሉ ትልቅ ስለሆነ ነው።

የባለሞያዎቹ ቡድን ብላክ ቦክሱ የያዘውን መረጃ በመተንተን ለአውሮፕላኑ መከስከስ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ይለያሉ።

አውሮፕላን አብራሪ ሥነ ምግባር መጠበቅ አለበት። ከማንኛውም አይነት ሱስ የጸዳ፣ የአመጋገብ ሥርዓቱን ያስተካከለ፣ በቂ እንቅልፍ የሚተኛ እና አካላዊ እንቅስቃሴ የሚያደርግ መሆን ይገባዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደግሞ “በሥነ ምግባር መርህ ላይ አይደራደርም” ይላሉ ካፒቴን ተስፋይ።

ጥሩ የሠራ የሚበረታታበትና የሚያድግበት፣ ያጠፋ ደግሞ ያለ ምንም ማቅማማት የሚቀጣበት ተቋም መሆኑን ከካፒቴን ተስፋይ ንግግር መረዳት ይቻላል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብዙ አደጋዎች የማያጋጥሙትና ብዙዎች ከደህንነት አንጻር የሚመርጡት መሆኑ ይነገርለታል። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የአየር መንገዱ ሠራተኞች መልካም ሥነ ምግባር መሆኑን ካፒቴን ተስፋይ ይናገራሉ።

ካፒቴን ተስፋይ ደስተኛ ጊዜያትን እንዳሳለፉ ሁሉ በጣም ያዘኑበት ወቅትም አለ።

በተለይም በአጋቾች ምክንያት ኮሞሮስ ደሴት ላይ የተከሰከሰውን አውሮፕላን እንዲሁም ከሌባኖስ ቤይሩት ከተነሳ በኋላ አደጋ የደረሰበትን አውሮፕላን ይጠቅሳሉ።

ከሁሉም በላይ ግን በቅርቡ ቢሾፍቱ ላይ የተከሰከሰው አውሮፕላን ያስታውሳሉ። በተለይ ደግሞ አብራሪዎቹ ምንም ማድረግ የማይችሉበት ሁኔታ በመከሰቱ ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

አደጋው በደረሰበት አውሮፕላን የነበረው ዋና ፓይለት አብሮዋቸው ረዳት ሆኖ ይሠራ እንደነበር አስታውሰው፤ “በጣም ጎበዝና ትልቅ ተስፋ የነበረው ወጣት ነበር” ሲሉ ይገልጹታል።

‘ቆይ ቦምእንድረስና እንተያያለን”

ካፒቴን ተስፋይ አውሮፕላን አስነስተው ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፍያ ወደ ቦምቤ ሕንድ እያመሩ ነው።

አብዛኛዎቹ ተሳፋሪዎች የምዕራብ አፍሪካ ሰዎች ናቸው። አንድ ናይጄርያዊ እና ሕንዳዊ ተጣልተው አውሮፕላኑ ተበጠበጠ። ካፒቴኑ መንገደኞቹን ማረጋጋት ያዙ። ‘አንተም ተው አንተም ተው’ ግልግል ገቡ። አረጋጉት።

ናይጄርያዊው “ቆይ ቦምቤ እንድረስና እንተያያለን” ብሎ ዝቶ ወደ ወንበሩ ተመልሶ ጉዟቸውን መቀጠላቸውን ያስታውሳሉ።

ጠጥቶ አውሮፕላን መሳፈር የተከለከለ ነው። ቢሆንም ሰክሮ መጨፈር የሚዳዳው አይታጣም። ጉዞ መሀል ላይ ብድግ ብሎ “አወርዱኝ” የሚልም ሞልቷል።

ካፒቴኑ እንደነገሩን፤ ትንሽ ብልሽት ስላጋጠመን አስተካክለን ጉዟችንን እንቀጥላለን ሲባል፤ “ድሮም አልጣመኝም። አውርዱኝ!” ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚልም በብዛት ያጋጥማል።