ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮ-ኤርትራ ስምምነትና የፕሬዝደንት ኢሳያስ ጉዞዎች
የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለሁለት አስርት ዓመታት ሰላምም ሆነ ጦርነተ የሌለበት ሁኔታ ተቀይሮ በአገራቱ መካከል ሰላም ሰፍኗል።
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የሁለቱ አገራት መሪዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ከአንዳቸው ወደ ሌላኛው አገር ለሥራ ጉብኝት ተደጋጋሚ ጉዞ አድርገዋል።
የሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝታቸውን ዛሬ ያተናቀቅቃሉ ተብሎ የሚጠበቀው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሁለቱ አገራት መካከል የሰላም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ቢያንስ ለስድስት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ አምርተዋል።
በእነዚህ ጉብኝቶች በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩሩ በደፈናው ከመጥቀስ በዘለለ የተደረጉ ውይይቶች የተደረጉ ቢሆንም አስካሁን በይፋ በዝርዝር የተነገረ ጉዳይ የለም።
ለመሆኑ ፕሬዝደንት ኢሳያስ ወደ ኢትዮጵያ መቼ መጡ?
ቅዳሜ ሐምሌ 7/2010 ዓ.ም [14/7/2018]
ፕሬዝደንት ኢሳያስ ከሃያ ዓመታት በላይ ከሚሆን ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ሐምሌ 7/2010 ዓ.ም ነበር።
ፕሬዝደንት ኢሳያስ ወደ ኢትዮጵያ ከምምጣታቸው በፊት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕምድ የሁለቱ አገራትን የሰላም ሂደት ለማስጀመር ሐምሌ 1 ቀን 2010 ላይ ወደ አሥመራ ማቅናታቸው ይታወሳል።
ፕሬዝደንት ኢሳያስ ከ20 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ ጉብኘት ለማድረግ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ሲደርሱ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ፕሬዝደንቱ በዚህ ጉብኝታቸው ነበር ለሃያ ዓመታት ተዘግቶ የነበረውን የኤርትራ ኤምባሲ የከፈቱት። ይህም በሁለቱ አገራት መካከል ተቋርጦ የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መታደሱን በይፋ ያመላከተ ነበር።
ዓርብ ጥቅም 30/2011 ዓ.ም [9/11/2018]
ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለጉብኝት በታሪካዊቷ በጎንደር ተገኙ።
ፐሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ የአማራ ክልልን ለመጎብኘት በጎንደር ተገኝተው ነበር።
መሪዎቹን ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በጎንደር ተገኝተው አቀባብል አድርገውላቸዋል። መሪዎቹ በቆይታቸው ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን የጎንደር ቆይታቸውን አጠናቀው ወደ በባሕር ዳር ከተማም አቅንተውም ነበር።
ማክሰኞ መስከረም 1/2011 [11/09/2018]
በዘመን መለወጫ ዕለት ፕሬዝደንት ኢሳያስ እና ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በሁለቱ አገራት አዋሳኝ ድንበር ላይ ተገናኝተው ኤርትራንና ኢትዮጵያ ከሚያገናኙት ሁለቱን የደንበር በሮች ማለትም ደባይሲማ-ቡሬ እና ሰርሐ-ዛላምበሳን ከ20 ዓመታት በኋላ ከፈቱ።
የድንበሮቹን መከፈት ተከትሎ 'የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዝምድና ሰላማዊ መልክ ለማስያዝ ባደረጉት አስተዋጽኦ' በሚል የሳዑዲ አራቢያ መንግሥት "የንጉሥ አብደልአዚዝ ኒሻን" ሽልማትን ለሁለቱ መሪዎች አበረከተላቸው።
እሁድ ሚያዚያ 25/ 2012 [3/05/2020]
በዕለተ እሁድ ሚያዚያ 25/2012 ዓ.ም ፕሬዝደንት ኢሳያስ ለሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ ተገኝተው ነበር።
የውጭ ጉዳይ ሚንስትራቸውንና አማካሪያቸውን አስከትለው አዲስ አበባ የገቡት ፕሬዝደንቱ፤ የጉብኝታቸው ዓላማ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን እንዲሁም የበረሃ አንበጣን ለመዋጋት ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር መምከር አንዱ መሆኑ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
የኤርትራው የማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገብረመስቀል፤ ሁለቱ መሪዎች የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት ሁኔታ ላይ ይወያያሉ ሲሉ በወቅቱ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረው ነበር።
ሰኞ ጥቅምት 2/2013 [12/10/2020]
ፕሬዝደንት ኢሳያስ ለሶስት ቀናት ጉብኝት ከትናንት በስቲያ ጅማ መግባታቸው ይታወሳል። ፕሬዝደንት ኢሳያስ በዚህ ጉብኝታቸው የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በደቡብ ክልል ውስጥ እተገነባ ያለ የኃይል ማመንጫን ጎብኝተዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል የሰላም ስምምት ከተደረሰ በኋላ ፕሬዝደንት ኢያሳያስ አፈወርቂ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በቀጠናው ወደሚገኙ የተለያዩ አገራትም በመጓዝ የሚያደርጉት የሥራ ጉብኝት ጨምሯል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ፕሬዝደንት ኢያሳያስ ወደ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ግብጽ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ተጉዘዋል።
ኤርትራ እና ሶማሊያ
ኤርትራ ነጻነቷን ከተጎናጸፈች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሬዝደንት ኢሳያስ ታህሳስ 4/2011ዓ.ም ወደ ሶማሊያ ተጉዘው ነበር።
በወቅቱ የሶማሊያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ፕሬዝደንት ኢሳያስ እና ፕሬዝደንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፈርማጆ የሁለትዮሽ ስምምነት ይፈርማሉ ሲል የዘግቦ ነበር።
ፕሬዝንት ኢሳያስ ሶማሊያን ሲጎበኙ ይህ የመጀመሪያቸው ነበር።
ፕሬዝደንት ኢሳያስ ወደ ሞቃዲሹ ከማምራታቸው በፊት ከሶማሊያው አቻቸው ጋር በአሥመራ እና አዲስ አበባ ተገናኝተው ነበር።
መስከረም 5/2011 ዓ.ም. የኢትዮጵያ፣ የሶማሊያ እና የኤርትራ መሪዎች በአሥመራ ከተማ የትብብር ስምምነት ፈርመው እንደነበረ እና የዚህን የትብብር ስምምነት አፈጻጸምን ለመገምገም መስከረም 29 እና 30 በአዲስ አበባ ተገናኝተው እንደነበረ የኤርትራ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።
ከዚህ በተጨማሪም ኤርትራ ሶማሊያን እና ራስ-ገዝ አስተዳደር የሆነችውን ሶማሊላንድን ለማሸማገል ፍላጎት እንዳላት በስፋት ሲዘገብ ቆይቷል።
ለሶማሊላንድ የሚወግነው 'ጋሮዌኦላይን' የተባለው የድረ ገጽ ዜና ምንጭ ኤርትራ ሁለቱን አካላት ለማሸማገል ለመሪዎቹ ጥያቄ ስለማቅረቧ ዝርዝር ዘገባ አስነብቦ ነበር።
ከኤርትራ በተጨማሪ አሜሪካ እንዲሁም የአውሮፓ ሕብረትን ጨምሮ ሌሎች የቀጠናው አገራት የሶማሊያን ፌደራል መንግሥትን እና ፑንትላንድን ለማሸማገል ፍላጎት ስለማሳያታቸው የሶማሊያን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ጠቅሶ ጋርዌኦላይን ዘግቧል።
መስከረም 24/2013 የሶማሊያው ፕሬዝደንት በአሥመራ ተገኝተው ነበር። የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገ/መስቀል ፕሬዝደንት ኢሳያስ እና ፕሬዝደንት ሞሐመድ ፈርማጆ ሰፊ ውይይት ማካሄዳቸውን ጠቁመው፤ በአሥመራ የተደረሰውን ስምምነትን አጠናክር ለማስፈጸም መስማማታቸውን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ኤርትራ እና ኬንያ
ፕሬዝደንት ኢሳያስ ታህሳስ 2011 ዓ.ም ላይ የሱማሊያ ጉብኝታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ያቀኑት ወደ ኬንያ ነበር።
ሁለቱ የምስሥቅ አፍሪካ አገራት ያላቸው ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ትስስር እዚህ ግባ የሚባል አልበረም። ኬንያ በአሥመራ ኤምባሲ የላትም። ጉዳዮቿንም የምታስፈጽመው ካይሮ በሚገኝው ኤምባሲዋ በኩል ነው።
እአአ 2011 ላይ የኬንያው የውጭ ሚንስቴር ኤርትራ በሱማሊያ ለሚንቀሳቀሰው አል-ሸባብ የትጥቅ ድጋፍ ታደርጋላች ብሎ መክሰሱን ሮይተርስ ዘግቦ ነበር።
የአሁኑ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያት አሥመራን በቅርቡ ከመጎብኘታቸው በፊት ኤርትራን የጎበኙት የመጨረሻው የኬንያ ፕሬዝደንት ዳንኤል አራፕ ሞይ ነበሩ። እአአ 1996 ላይ የወቅቱ ኬንያ ፕሬዝደንት በአሥመራ የነበራቸው ቆይታ ከሰዓታት የዘለለ አልነበረም።
ፕሬዝደንት ኢሳያስ ወደ ኬንያ ያመሩት ከፕሬደዝንት ኡሁሩ ኬንያት በቀረበላቸው ግብዣ ነበር። በኬንያ ብሔራዊ ደኅንነት ዳይሬክተር ጀነራል የተመራ ልዑክ ወደ አሥመራ ባቀናበት ወቅት ነበር ከፕሬዝደንት ኡሁሩ የተላከውን ግብዣ ያቀረበው።
ታህሳስ 6/2011 ዓ.ም ፕሬዝደንት ኢሳያስ ናይሮቢ የገቡት ለሁለት ቀናት ጉብኝት ነበር። ፕሬዝደንቱ በቆይታቸው ከኬንያው አቻቸው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ጋር "በሁለቱ አገራት መካከል የንግድ ግንኙነትን ማጠንከር" የሚለው ትልቁ አንጀንዳ እንደነበረ የኤርትራ ቴሌቪዥን ዘግቦ ነበር።
ሚያዚያ 25/2011 ዓ.ም ላይ ደግሞ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ወደ አሥመራ ተጉዘው ነበር። ከፕሬዝደንት ኡሁሩ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድም በአሥመራ ተገኝተው መሪዎቹ የሦስትዮሽ ምክክር አድርገዋል።
ኤርትራ እና ሱዳን
ከዚህ ቀደም ኤርትራ እና ሱዳን በተለያዩ አጋጣሚዎች ይወቃቀሱ ነበር።
እአአ 2005 ላይ ሱዳን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት፤ ኤርትራ በምሥራቅ ሱዳን ለሚገኙ ታጣቂዎች የቁሳቁስ ድጋፍ ታደርጋለች ስትል ከሳ ነበር። ኤርትራ በበኩሏ ይህን የሱዳን መንግሥት ክስን አጣጥላለች።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግነኙነት እየታደሰ ይገኛል።
የሱዳኑ ፕሬዝደንት ኦማር አል-በሽር ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ሚያዚያ 2012 ላይ ፕሬዝደንት ኢሳያስ ወደ ሱዳን ተጉዘው ነበር።
በድጋሚ ሰኔ 13/2012 በሱዳን መዲና ካርቱም ተገኝተው ነበር። ፕሬዝደንቱ በጉብኝታቸው ወቅት ከሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ሌተናል ጀነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን ጋር ተገናኝተዋል።
ሁለቱ መሪዎች በሁለትዮሽ ጉዳዮች እንዲሁም በቀጠናው ሰላም ዙሪያ ምክክር አድርገው ነበር።
ጳጉሜ 2/2012 ዓ.ም ላይ ደግሞ ሌተናል ጀነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን ለአንድ ቀን ይፋዊ ሥራ ጉብኝት አሥመራ ተገኝተው ነበር።
የኤርትራ የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር የማነ ገ/መስቀል ሌተናል ጀነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን እና ፕሬዝደንት ኢሳያስ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ በሁለቱ አገራት ፍላጎቶች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል ብለዋል።
ሐምሌ 2012 ላይ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌህ በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በግብጽ መካከል በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያለውን አለመግባባት ለማጥረት ኤርትራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን አያደረገች ነው ብለው ነበር።
ኤርትራ እና ግብጽ
መስከረም 13/2011 ላይ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ የግብጹን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚ ሸኩሪን በቤተ-መንግሥታቸው ተቀብለው ማነጋገራቸውን የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር።
በቀጣናው ሰላም እና ትብብር ስለማስፈን እንዲሁም የሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ስምምነት ዙሪያ ውይይት ማካሄዳቸው ተጠቁሟል።
ሰኔ 28/2012 ዓ.ም ደግሞ ፕሬዝደንት ኢሳያስ ወደ ግብጽ ካይሮ ለሦስት ቀናት አምርተው ነበር።
ፕሬዝደንት ኢሳያስ በካይሮ ቆይታቸው ከፕሬዝደንት አብድል ፋታህ አል-ሲሲ እና ከሌሎች የግብጽ ባለስልጣናት ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ኤርትራ ቴሌቪዥን ዘግቦ ነበር።
ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን
ሚያዚያ 25/2011 ላይ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ አሕምድ እና ፕሬዝደንት ኢሳያስ በአሥመራ ከተገናኙ በኋላ በቀጣዩ ቀን ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ወደ ደቡብ ሱዳን አምርተዋል።
ፕሬዝደንት ኢሳያስ እና ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ሚያዚያ 26/2011 ለአንድ ቀን የሥራ ጉብኝት ጁባ ከደረሱ በኋላ ከፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ጋር በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ የሦስትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
የኤርትራ ግንኙነት መሻሻል
ኢትዮጵያና ኤርትራ ደም አፋሳሽ የድንበር ጦርነት ካካሄዱ በኋላ ኤርትራ በአካባቢዊ፣ በአህጉራዊና በዓለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ የነበራት ተሳትፎ ከመቀዛቀዙ በተጨማሪ ማእቀቦችም ተጥለውባት ቆይተዋል።
በእንዲህ ያለው ሁኔታ ከኢትዮጵያ ጋር በፍጥጫ ከሌሎች አገራት ጋር ደግሞ በጥርጣሬ ውስጥ ለ20 ዓመታት ያህል የቆችው ኤርትራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ስልጣን መጥተው በሁለቱ አገራት መካከል የሰላም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ኤርትራ ከጂቡቲ በስተቀር ከአካባቢው አገራት ጋር ያላት ግንኙነት መጠናከርን ያሳየ ይመስላል።
ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ያታው ለውት ምናልባትም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ለዓመታት የቆየችበት ፍጥጫ ከሌሎች አገራት ጋር በነበራት ግንኙነት ላይ ጥላውን አጥልቶበት ቆይቷል ለማለት ያስደፍራል።