ተመድ፡ “የከፋ የአየር ንብረት ለውጥ ከመከሰቱ በፊት ማስጠንቀቂያ ያስፈልጋል”

ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያስከትል የአየር ሁኔታ ከመከሰቱ በፊት ማስጠንቀቂያ እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አስታውቋል።

ድርጅቱ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ የከፋ የአየር ሁኔታ ከመከሰቱ በፊት ማስጠንቀቂያ የሚሰጥበት መንገድ እንዲኖር አገራት ገንዘብ ፈሰስ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ባለፉት 50 ዓመታት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የተፈጥሮ አደጋዎች እየተበራከቱ ነው።

ዓለም ላይ ከሦስት ሰዎች አንዱ/አንዷ የአየር ሁኔታ ማስጠንቀቂያ እንደማይደርሳቸው ጥናት ያሳያል።

በቀጣይ አሥር ዓመታት በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት እርዳታ የሚሹ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ ይጨምራል ተብሎ ይገመታል።

በጥናቱ ከ16 ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ከዓለም አቀፉ የአየር ሁኔታ ትንበያ ተቋም የተወጣጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

ባለፉት 50 ዓመታት ከአየር ሁኔታ፣ ከአየር ንብረት ለውጥ እና ከውሃ አካል ጋር የተያያዙ 11 ሺህ አደጋዎች ተከስተው፤ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች ሞተዋል። ምጣኔ ሀብትም የ3.5 ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ ገጥሞታል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2018፤ 108 ሚሊዮን ሰዎች ተፈጥሯዊ አደጋ ከፈጠረባቸው ጫና ለመላቀቅ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ድጋፍ ጠይቀዋል።

የተመድን ሪፖርት የጻፉት ባለሙያዎች፤ በ2030 እርዳታ የሚሹ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ አድጎ፤ ምጣኔ ሀብት ላይ የሚያሳድረው ጫና በዓመት 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ያስረዳሉ።

“የከፋ የአየር ሁኔታ ከመምጣቱ በፊት ማስጠንቀቂያ ያስፈልጋል”

ተመድ እንደሚለው፤ የከፋ የአየር ሁኔታ ከመከሰቱ በፊት በተገቢው መንገድ ማስጠንቀቂያ መሰጠት አለበት። ይህም የአየር ሁኔታ ምን እንደሚመስል ከመተንበይ ባለፈ፤ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ያካተተም መሆን ይገባዋል።

ማስጠንቀቂያዎች በታዳጊ አገራት እንዲሁም በደሴቶች የበለጠ አስፈላጊ ናቸው።

እነዚህ አገራት ባለፉት አምስት አሠርታት ከአየር ሁኔታና የአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ አጥተዋል።

ከተፈጥሮ አደጋ ጋር በተያያዘ ከተከሰቱ ህልፈቶች 70% የተከሰቱት በድሃ አገራት ነው።

የዓለም አቀፉ የአየር ሁኔታ ትንበያ ተቋም እንደሚለው፤ አፍሪካ ውስጥ ካሉ የአየር ሁኔታ ትንበያ ተቋሞች ደረጃቸውን የጠበቁት 26% ብቻ ናቸው።

ኮሮናቫይረስ የአየር ሁኔታ ማስጠንቀቂያ ላይ ጫና ማሳደሩን የድርጅቱ ሪፖርት ይጠቁማል።

ሆኖም ግን የአየር ንብረት ለውጥ ተፈጥሯዊ አደጋ እያስከተለባቸው ያሉ ድሃ አገራት መረሳት እንደሌለባቸውም ተገልጿል።

የዓለም አቀፉ የአየር ሁኔታ ትንበያ ተቋም ዋና ጸሐፊ ፕ/ር ፔትሪ ታላስ “ዝግጁ ሆኖ በተገቢው ጊዜ፣ በተገቢው ቦታ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። የሰዎችን ሕይወትና ቤት ንበረታቸውን ለመታደግ ያስችላል” ሲሉ ገልጸዋል።

አያይዘውም፤ “ኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ የጤና ሥርዓትና ምጣኔ ሀብትንም አቃውሷል። ከዚህ ለማገገም ዓመታት ይወስዳል። የአየር ንብረት ለውጥ ለዘመናት በሰው ልጆች፣ በሥነ ምህዳር፣ በምጣኔ ሀብት ላይ ዘላቂ ተጽዕኖ እንዳለው መረሳት የለበትም” ብለዋል።

በተመድ የአደጋ ቅነሳ ክፍል ልዩ ተወካይ ማሚ ሚዙቶሪ እንዳሉት፤ ኮቪድ-19 ያመጣው የአደጋ ጊዜ ርብርብ ዓለምን ከአየር ንብረት ለውጥ ለመታደግም መተግበር አለበት።

ምን ይደረግ?

በተመድ ሪፖርት መሠረት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ስድስት ነጥቦች ቀጣዮቹ ናቸው፦

  • አፍሪካ ውስጥና በትንሽ ደሴቶች የከፋ የአየር ሁኔታ ከመከሰቱ በፊት ማስጠንቀቂያ የሚሰጥበት ስርዓት ገንዘብ ሊመደብለትና ሊሻሻል ይገባል።
  • ቅድመ ማስጠንቀቂያን ወደ ተግባር በመቀየር ረገድ ገንዘብ ይመደብ።
  • ዓለም አቀፉ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዘላቂነት ያለው የገንዘብ ድጋፍ ያሻዋል።
  • ለቅድመ ማስጠንቀቂያ የሚመደቡ በጀቶች የት እንደተመደቡ፣ ምን ውጤት እንዳስገኙ ክትትል ያስፈልጋል።
  • የአየር ሁኔታ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዘላቂነትና ውጤታማነቱ መገምገም አለበት።
  • በተለይም በታዳጊ አገራትና በደሴቶች ላይ ያለው የመረጃ ክፍተት መሞላት አለበት።