በባሌ በፖሊስ ተገደለ የተባለው ወጣት ጉዳይ እየተመረመረ መሆኑ ተገለጸ

ባለፈው እሑድ ጥቅምት 1 ቀን 2013 ዓ. ም. ባሌ ሮቤ ውስጥ ሰላማዊ ሰልፍ እያካሄዱ በነበሩ ወጣቶች ላይ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ አንድ ወጣት ከተገደለ በኋላ ጉዳዩ እየተመረመረ መሆኑ ተገለጸ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዓይን እማኞች እንዲሁም የሮቤ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ደጀኔ ወጣቱ መገደሉን አረጋግጠዋል፤ ክስተቱ ሰልፍ ሳይሆን በከተማው ረብሻ ለመፍጠር የተደረገ ሙከራ ነው ሲሉ ከንቲባው ተናግረዋል።

ሰልፉ ላይ ከተሳተፉት አንዱ የሆነና ስሙ እንዲገለጽ ያልፈለገ ወጣት ለቢቢሲ እንደገለጸው፤ ከጠዋቱ 3 ሰዓት እስከ 4 ሰዓት ገደማ ከ15-20 የሚጠጉ ወጣቶች በሮቤ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ሲያካሂዱ ነበር።

"ሰልፉ ላይ ጀዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባ ይፈቱ የሚልና በኦሮሚያ ግድያ መቆም አለበት የሚሉ መፈክሮቸን እያሰማን ነበር" ብሏል ወጣቱ።

ሰላማዊ ሰልፉ ከተጀመረ ከ30 ደቂቃ በኋላ ግሪን ካፌ ተብሎ በሚጠራ ቦታ ላይ "የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ከኋላ መጥቶ ከበበን። ከዚያም ተኩስ ከፈቱብን። ሰልፉን በተኑ። ልጁ የተገደለው ያኔ ነው። ይሄን ልጅ መግደላቸው ሕብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ቁጣና ሀዘን ፈጥሯል" ሲልም የተከሰተውን አስረድቷል።

ሌላው ስሜ አይጠቀስ ያለን የዓይን እማኝ፤ ወጣቱ በተገደለበት ወቅት እሱም ግራ እጁን በጥይት መመታቱን ተናግሯል።

በቦታው ከ10 እስከ 15 የሚሆኑ ወጣቶች እንደነበሩ የገለጸው ወጣት "ፖሊሶች ከኋላችን መምጣታቸውን አየን። ከአውራሪስ ሰፈር ተነስተን፣ በአረጎው መናሀርያ ጋር አልፈን ግሪን ካፌ ጋ ደረስን። እዛ ስንደርስ ነው ፖሊሶቹ ከኋላችን መምጣታቸውን ያየነው" ሲል ክስተቱን ተናግሯል።

"ፖሊሶቹ ተኩስ ሲጀምሩ መሮጥ ጀመርን። እኔም ሮጬ ዘልዬ የሆነ ሱቅ ውስጥ ገባሁ። ግራ እጄን፣ ከክንዴ በላይ በጥይት መመታቴን የተረዳሁት ያኔ ነው" ሲልም አክሏል።

የሮቤ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ደጀኔ አንድ ወጣት መገደሉን አምነው፤ ጉዳዩ በምርመራ ላይ እንደሚገኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ሁኔታውን ሰልፍ ብሎ ለመጥራት ያስቸግራል። ምክንያቱም ቁጥራቸው ከ10 እስከ 15 ቢሆን ነው" ያሉት አቶ ገዛኸኝ ደጀኔ፤ "ረብሻ ለመፍጠር ሙከራ እንዳደረጉ ነው የምንረዳው። እነዚህ ወጣቶች ተደራጅተው ድምጽ እያሰሙ ለረብሻ ቅስቀሳ እያደረጉ ነበር። በወቅቱ የጸጥታ ኃይል በቦታው ስለነበር ቶሎ ማስቆም ችሏል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰራጨ አጭር ቪዲዮ ፖሊስ ሲተኩስ እንደሚያሳይ በመጥቀስ፤ የጸጥታ ኃይል ሁኔታውን አረጋጋ የሚባለው እንዴት ነው? ወጣቶቹ ቁጥራቸው ትንሽ ሆኖ ሳለ ለምን ተኩስ መክፈት አስፈለገ? ተብለው የተጠየቁት ከንቲባው፡

"በቦታው የጸጥታ ኃይል ስላለ የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና ሁኔታውን ለማረጋጋት እርምጃ ወስዷል። በዚህም የደረሰ ጉዳት አለ። የችግሩን ክብደት የሚወስነው በቦታው የነበረው የጸጥታ አካል እንጂ እኔም ሆንኩ ሌላ አይደለም" ሲሉ አቶ ደጀኔ መልሰዋል።

ከንቲባው አያይዘውም፤ "ምናልባት ሊመጣ ይችል የነበረውን ችግር ለማስቀረት እርምጃ ወስዶ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ሁኔታው ምርመራ ላይ ስለሆነ ከዚህ በላይ ለመናገር አሁን ይከብዳል። ምርመራው ሲያልቅ ለሕዝብ ግልጽ እናደርጋለን" ብለዋል።

በደገም የተከሰተው ምንድን ነው?

በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ደገም ወረዳ ውስጥ ትናንት ማታ ከምሸቱ 6 ሰዓት አካባቢ አንድ ሾፌር ባለታወቁ ሰዎች መገደሉ ተሰምቷል።

በተጨማሪም ሦስት ሰዎች መቁሰላቸውን የዞኑ አስተዳደርና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አጥናፉ በቀለ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ክልል በመሄድ ላይ የነበሩ የከባድ መኪና ጭነት አሽከርካሪዎች ላይ አደጋው መድረሱን የምተናገሩት ኃላፊው፤ የተወሰኑት ተጎጂዎች ደግሞ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ላይ ነበሩ ናቸው ብለዋል።

አቶ አጥናፉ እንዳሉት፤ ጥቃቱ የደረሰው ከምሽቱ 6 ሰዓት አካባቢ ነው።

"የሞተው አንድ ሾፌር ሲሆን ሌሎች 3 ሾፌሮች ደግሞ በዱላ ተደብድበዋል። በጥይትም የተመቱ አሉ። ይህ ክስተት ከዚህ ቀደም አጋጥሞን አያውቅም። አሁን ሕዝቡ መንገድ እየጠበቀ ነው ያለው" ሲሉ አስረድተዋል።

ኃላፊው አያይዘውም፤ "ጥቃቱን ያደረሰው አካል ለጊዜው አይታወቅም። ፖሊስ ጉዳዩን እያጣራ ነው። ሆኖም ግን አጥቂዎቹ ዝርፊያ ለማካሄድ ጥቃቱን እንደፈጸሙ የሚያመለክቱ ነገሮች አሉ" ብለዋል።