ኮሮናቫይረስ ፡ ሕንድ የሰራችው አዲሱ የኮቪድ-19 መመርመሪያ

በሕንድ የተመራማሪዎች ቡድን ርካሽ የሆነ እና ወረቀት ላይ ቫይረሱን መለየት የሚያስችል የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ ተሰራ።
ይህ የኮቪድ-19 መመርመሪያ ዘዴ እርግዝናን በቀላሉ ለመመርመር እንደሚያገለግለው መሳሪያ ያለ ነው ተብሏል።
ተመራማሪዎች መርመሪያው በአንድ ሰዓት ውስጥ ውጤትን ማሳወቅ ይችላል ያሉ ሲሆን፤ ዋጋውም ከ 500 ሩፒ [የሕንድ ገንዘብ] ወይም 250 ብር ገደማ እንደሆነ አረጋግጠዋል።
የመመርመሪያ መሳሪያው በሕንዱ ኩባንያ ታታ የሚመረት ሲሆን በዓለምም ላይ የመጀመሪያው ወረቀትን መሰረት ያደረገ የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ ሆኖ ይመዘገባል።
የሕንድ መንግሥት ሳይንሳዊ ጉዳዮች አማካሪ ፕሮፌሰር ኬ ቪጄይ ራግሃቫን ለቢቢሲ "ቀላል፣ ምርጥ፣ አስተማማኝ፣ በቀላሉ ሊስፋፋ የሚችል፣ ወጪ ቆጣቢ ምርመራ" ብለውታል።
ይህ ፌሉዳ የተሰኘው መመርመሪያ ዘዴ የተሰራበት የምርምር ተቋም ውስጥ የሚሰሩ ተመራማሪዎች በ2000 ህሙማን ላይ ምርመራ አድርገዋል።
በዚህም ውጤታማነቱ ከ95 በመቶ በላይ መሆኑን ተናግረው፣ ቫይረሱ ያለበት ማንኛውንም ሰው በዚህ መሳሪያ መመርመር እንደሚቻል ተናግረዋል።
በዚህ መመርመሪያ መሳሪያ በቅድሚያ ማረጋገጥ ተፈልጎ የነበረው ስህተት የሆኑ የምርመራ ውጤቶች እንዳይገኙ የሚል ነበር። ይህንንም ፈተና አልፎ የሕንድ መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ለገበያ መቅረብ ይችላል ሲል ማረጋገጫ ሰጥቶታል።
በሕንድ ስድስት ሚሊዮን ያህል ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሲሆን፤ ይህም አገሪቱን በዓለም በቫይረሱ ከተጎዱ አገራት መካከል ሁለተኛዋ ያደርጋታል። እስካሁን ድረስ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች በወረርሽኙ ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ሕንድ በአሁኑ ጊዜ በቀን ሚሊዮን ናሙናዎችን እየመረመረች ሲሆን በመላው አገሪቱ ውስጥም 1ሺህ 200 ላቦራቶሪዎች ይገኛሉ።


















