ኮሮናቫይረስ፡ የአፍሪካ አገራት የኮቪድ-19 አንቲቦዲ ምርመራ ሊጀምሩ ነው

የሕክምና ባለሙያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሰባት የአፍሪካ አገራት የኮሮናቫይረስ አንቲቦዲ ምርመራ ሊጀምሩ መሆኑን የአፍሪካ በሽታ መቆጣጣርና መከላከል ማዕከል አስታወቀ።

ምርመራው ወረርሽኙ በአፍሪካ ውስጥ ምን ያህል እንደተሰራጨ ለማወቅ የሚደረግ ጥረት አካል ነው ተብሏል።

ድርጅቱ በሰተው ዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ "ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮን፣ ዛምቢያ፣ ዚምባብዌ፣ ካሜሮን፣ ናይጄሪያ፣ ሞሮኮ ምርመራውን ቀድመው ለማድረግ የተዘጋጁ አገራት ናቸው" ያሉት የአፍሪካ በሽታ መቆጣጣርና መከላከል የበላይ ኃላፊ ጆን ኬንጋሶንግ ናቸው።

ኃላፊው አህጉሪቱ እስካሁን ድረስ 9.4 ሚሊዮን የኮሮናቫይረስ ምርመራ ማድረጓን ገልፀው፤ 10 ሚሊዮን ምርመራዎችን ለማከናወን የታቀደውን ዕቅድ ለማሳካት ከአገራት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ዶ/ር ንኬንጋሶንግ አፍሪካ በክትባት ምርመር ረገድም ጥሩ መንገድ ላይ መሆኗን ተናግረዋል።

አክለውም በአህጉር ደረጃ ለሚደረግ ክሊኒካል ሙከራ ጥምረት ለማቋቋም ስትራቴጂ መቀረፁን ገልፀው፣ ለክትባቱ የሚያስፈልጉ አቅርቦቶችን ለመግዛት እና የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ይጀመራል ብለዋል።

እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ መረጃ ከሆነ በአፍሪካ እስካሁን ድረስ 1,084,904 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።

በአፍሪካ በብዛት የኮሮናቫይረስ ምርመራ ካደረጉ አገራት መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የምትይዘው ደቡብ አፍሪካ ነች።

ደቡብ አፍሪካ አህጉሪቱ ከመረመረቻቸው አጠቃላይ የኮሮናቫይረስ ምርመራዎች መካከል 80 በመቶውን መርምራለች ሲል የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል አስታውቋል።

ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል ሞሮኮ፣ ጋና፣ ግብጽ፣ ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ሞሪሺየስ፣ ኬንያ፣ ናይጄርያ እና ሩዋንዳ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን መርምረዋል።

ደቡብ አፍሪካ በኮሮናቫይረስ በተያዙ ሰዎች ቁጥርም ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ስትሆን ከዓለም ደግሞ አምስተኛዋ ነች።

ነገር ግን በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ከተጠቁ አገራት አንጻር ሲታይ በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር በደቡብ አፍሪካ በጣም ትንሽ ነው።

በርግጥ በአገሪቱ የሚገኝ አንድ በሕክምና ምርምር ላይ የተሰማራ ተቋም በአገሪቱ የተመዘገበው የሟቾች ቁጥር ከዚህም ሊልቅ እንደደሚችል አስታውቋል።

የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠር እና መከላከል ማዕከል የቫይረሱ ስርጭትን በቅርበት ከሚከታተልባቸው አገራት መካከል ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ዛምቢያ፣ ካሜሮን፣ ጋቦን፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ጋና፣ አይቮሪ ኮስት፣ ሴኔጋል ፣ ግብጽ፣ ሞሮኮ እና አልጄሪያ ይገኙበታል።

በመካከለኛው እና ምሥራቅ አፍሪካ ባሉ የአህጉሪቱ አገራት በጣም ዝቅተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተመዘገበ ሲሆን በሌሎች አገራት ደግሞ በአንጻራዊነት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎ መያዛቸው ተመዝግቧል።

እንደ አፍሪካ በሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል መረጃ ከሆነ በአህጉሪቱ የሚገኙ አምስት አገራት በአጠቃላይ በአህጉሪቱ በቫይረሱ መያዛቸው ከተገለፀው 75 እጁን ያህል መዝግበዋል።

ይህም በመላ አህጉሪቱ የቫይረሱ ስርጭት ምን እንደሚመስል ለማወቅ ያለውን ሁኔታ አዳጋች ማድረጉን የማዕከሉ ኃላፊዎች ይገልፃሉ።

ኮሮና
Banner