ኩዌት ፡ ኢሚር ሼክ ሳባህ አል አል አህመድ አል ሳባህ በ91 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

የኩዌቱ ኢሚር ሼክ ሳባህ አል አል አህመድ አል ሳባህ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኢሚር ሼክ ሳባህ አል አል አህመድ አል ሳባህ

የኩዌቱ ኢሚር ሼክ ሳባህ አል አል አህመድ አል ሳባህ በ91 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን የአገሪቱ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ዘግቡ።

በቦታቸውም የ83 ዓመቱ ወንድማቸው ልዑል አልጋ ወራሽ ሼክ ናዋፍ አል አሕመድ ይተካሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሐምሌ ወር ላይ ሼክ ሳባህ ምንነቱ ላልተገለፀ ሕመም በኩዌት ቀዶ ሕክምና ካደረጉ በኋላ፤ ለተሻለ ሕክምና ወደ አሜሪካ ሄደው ነበር።

ሼክ ሳባህ በነዳጅ ዘይት ሐብቷ የምትታወቀውን የአረብ ባሕረ ሰላጤዋን አገር ከ2006 ጀምሮ መርተዋል። ከ50 ዓመታት በላይም የባሕረ ሰላጤው አገራትን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲዎችን በመንደፍ ይወደሳሉ።

ከጎርጎሮሳዊያኑ 1990 እስከ 1991 ኩዌት በኢራቅ ኃይሎች በተወረረችበትና የባሕረ ሰላጤው ጦርነት ወቅት፤ ኢራቅን ሲደግፉ በነበሩ አገራት መካከል የነበረውን ግንኙነት ለመመለስ ባደረጉት ጥረትም 'የአረብ ዲፕሎማሲ ዲን' የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል።

ኢሚሩ አሁን በሳዑዲ አረቢያና ተባባሪዎቿ እንዲሁም በኳታር መካከል እየተካሄደ ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ጨምሮ በቀጠናው ለሚፈጠሩ አለመግባባቶችም እንደ ሽማግሌ በመሆን ይታወቃሉ።

ለዚህም አንዱ ማሳያ ኩዌት በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ጣልቃ ከመግባት ራሷን ማቀቧ ነው። ጣልቃ ከመግባት ይልቅ በርካታ ለሰብዓዊ እርዳታ የሚረዱ የድጋፍ ሰጭ ድርጅቶች ስብሰባዎችን በማዘጋጀት ነው የምትታወቀው።

ሼክ ሳባህ ሥልጣን ላይ የወጡት አሚር ሼክ ሳድ አል አብዱላህ ለዘጠኝ ቀናት ካገለገሉ በኋላ በጤና ምክንያት ሥልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ በጥር 2006 ነበር።

በቀድሞው ኢሚር ሼክ ጃበር አል አሕመድ አል ጃበር አል ሳባህ አስተዳዳር ስርም ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል። ለበርካታ ዓመታትም በይፋ ያልወጡ መሪ ተደርገው ይታዩ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን ከ1963 እስከ 1991 ድረስ እንዲሁም ከ1992 እስከ 2003 ድረስ አገልግለዋል።

3.4 ሚሊዮን የውጭ ዜጎችን ጨምሮ 4.8 ሚሊዮን የሚገመት የሕዝብ ብዛት ያላት ኩዌት በዓለማችን ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት ካላቸው አገራት ስድስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ዋነኛዋ የአሜሪካ አጋርም ናት።

ኩዌት ላላፉት 260 ዓመታት የተዳደረችው በሳባህ ንጉሣዊያን ቤተሰቦች ነው።

ኢሚር ሼክ ሳባህ በአገሪቱ አጠቃላይ የፖለቲካ ጉዳይ ላይ ሚና የነበራቸው ሲሆን፤ ሥልጣናቸው ምክር ቤቱን እስከ መሻር ወይም መበተን እንዲሁም ምርጫ ለማካሄድ ጥሪ እስከማቅረብ ድረስ ከፍ ያለ ነበር።