ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የታይላንድ ሆቴልን አንቋሿል የተባለው አሜሪካዊ ሊታሰር ይችላል ተባለ
በታይላንድ ቆይታው ወቅት ስላረፈበት ሆቴል አሉታዊ ነገሮችን መፃፉን ተከትሎ አንድ አሜሪካዊ ግለሰብ የሁለት ዓመት እስር ሊጠብቀው ይችላል ተብሏል።
ያረፈበት ሪዞርትም ጥብቅ በሚባለው የአገሪቱ ስም ማጥፋት ወንጀል ከስሶታል።
በታይላንድ ነዋሪ የሆነው አሜሪካዊው ዌስሊ ባርንስ በተለያዩ ድረገፆችም ላይ ሪዞርቱን "ዘመናዊ ባርነት የሚካሄድበት" በማለት ወንጅሎ ፅፏል።
ዘ ሲ ቪው ሪዞርት በበኩሉ እንግዳው ያቀረበው ትችት "መሰረት የሌለው፣ ሃሰትና የሆቴሉንም ስም በማጥፋትም ጉዳት አድርሷል ብለዋል።
በትሪፕ አድቫይዘር ድረገፅ ላይ ሆቴሉን አስመልክቶ የወጣው ፅሁፍ ፍትሃዊ እንዳልሆነ በማስመልከት ክስ የሆቴሉ ባለቤት መመስረቱንም ፖሊስን ዋቢ አድርጎ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
ይህን ሁሉ ክስና ውዝግብ ያስነሳው ኮህ ቻንግ በምትባለው ደሴት ውስጥ የሚገኘው ሪዞርት ውስጥ ያረፈው ዌስሊ የራሴን መጠጥ ማስገባት አለብኝ በሚል ከሆቴሉ አስተዳደር ጋር እሰጣገባ በመግባቱ ነው።
ግለሰቡ የሆቴሉን ተስተናጋጆች እንደረበሸና መጠጥ የሚያስገባም ከሆነ ክፍያውን ፈፅም ቢባልም እምቢተኝነት ማሳየቱን ሆቴሉ ባወጣው መግለጫው አትቷል።
ሆቴሉን ለቅቆ ከወጣም በኋላ በተደጋጋሚ አሉታዊ ነገሮችን ስለሆቴሉ መፃፉንም ተከትሎ ሆቴሉም በስም ማጥፋት ወንጀል ከሶታል።
ግለሰቡም በቁጥጥር ስር ውሎም ለሁለት ምሽቶች በእስር ቤት ያሳለፈ ሲሆን በዋስም ተለቅቋል።
አሜሪካዊው ግለሰብ በስም ማጥፋት ክስ ወንጀል ጥፋተኛም ሆኖ ከተገኘ እስከ ሁለት አመት የሚቆይ እስር ይጠብቀዋል ተብሏል።
ከዚህም ጋር በተያያዘ ስራውን ያጣው ግለሰብ ጉዳዩ የበለጠ ከገፋም ሌላ ስራ ለማግኘት እንደሚቸገር ለቢቢሲ ተናግሯል።
የፍርድ ሂደቱም ጥቅምት ወር ላይ ይጀምራል ተብሏል።