ደጋፊዎችን የወሩ መጨረሻ ላይ ወደ ስታዲየም የመመለሱ እቅድ ውድቅ ሆነ

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን ጨምሮ በእንግሊዝ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ላይ ደጋፊዎችን ከመስከረም 21 ጀምሮ ወደ ስታዲየም የማስገባቱ እቅድ ወድቅ መደረጉ ተገለጸ።

ይህ የሆነበት ምክንያት በዩናይድ ኪንግደም እና በተቀሩበት የአውሮፓ አገራት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ መሆኑን የጠቅላይ ሚንስትሩ ካቢኔ አባል የሆኑት ማይክል ጎብ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የነበረው እቅድ እስከ 1ሺህ የሚደርሱ ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም ገብተው ክለባቸውን እንዲደግፉ መፍቀድ ነበር።

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አርሰናል ከሼፊልድ ዩናይትድ መስከረም 23 በሚያደርጉት ጨዋታ ደጋፊዎች ወደ ስታዲየሞች ይገባሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

ካለፈው መጋቢት ወር ወዲህ በእንግሊዝ የእግር ኳስ ውድድሮች በዝግ ስታዲየም ሲካሄዱ ቆይተዋል።

በኮቪድ-19 ስርጭት ምክንያት ስፓርታዊ ውድድሮች በዝግ ስታዲየም እንዲደረጉ መወሰኑ በክለቦች ላይ ከፍተኛ የፋይንስ ቀውስ አስክትሏል።

የባህል፣ ሚዲያ እና ስፖርት ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ጁሊያን ናይት “ታዳሚዎች ወደ ስታዲየሞች የሚመለሱበትን ብልህ የሆኑ አሰራሮች ካልዘረጋን የስፖርት እና ባህላዊ መሠረተ ልማቶቻችን ተንኮታኩተው ይቀራሉ” ብለዋል።

ከ100 በላይ የስፖርታዊ ውድድሮች አመራሮች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ካጋጠማቸው ኪሳራ ለማገገም ለጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው በደብዳቤ ጠይቀዋል።

ስፖርት ኢንግላንድ የተሰኘው የመንግሥት አካል 200 ሚሊዮን ፓውንድ ለአስቸኳይ ወጪ መሸፈኛ በሚል ለስፖርት ክለቦች ድጋፍ አቅርቧል። ይሁን እንጂ ይህ ገንዘብ ክለቦች ያጋጠማቸውን ኪሳራ ለመሸፈን በቂ አይደለም ተብሏል።