ምርጫ 2013፡ የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እንዲካሄድና ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ወሰነ

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተራዝሞ የነበረው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ስብሰባው ወሰነ።

ምክር ቤቱ በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ አስቸኳይ ስብሰባው ለስድስተኛ ጊዜ የሚካሄደው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ የዓለም ጤና ድርጅትና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባስቀመጡት ምክረ ሃሳብ መሰረትም ቫይረሱን ለመካላከል የሚያስችሉ እርምጃዎችን በመውሰድ እንዲከናወን ወስኗል።

ይህም የውሳኔ ሐሳቡ በአንድ ተቃውሞና በስምንት ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ እንደፀደቀም ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ጠቁሟል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ ከኮሮናቫይረስ መከሰት በኋላ የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር በሚል ተከልክለው የነበሩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲጀመሩ እንዲሁም ተዘግተው የከረሙ ትምህርት ቤቶችም እንዲከፈቱ ወስኗል።

የውሳኔ ሐሳቡና ሪፖርቱን ያቀረቡትም የሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አበባ ዮሴፍ ናቸው።

ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምላሽ አሰጣጥና ቀጣይ እርምጃዎችን በተመለከተ ምክር ቤቱ መስከረም 8/ 2013 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ምርጫው ከጥንቃቄ ጋር መደረግ ይችላል የሚል ምክረ ሐሳብ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩል ቀርቦለት ነበር።

ይህንንም ሪፖርትና ምክረ ኃሳብ ለሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተባባሪነት ለሕግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መመራቱ ይታወሳል።

ምርጫው እንዲካሄድ ምክር ቤቱ ዝግጅት እንዲጀመረው ከመወሰኑ ውጪ መቼ እንደሚሆን የተሰጠ መረጃ የለም።

ምክር ቤቱ በተጨማሪ በዛሬው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ያቀረቧቸውን የአራት ሚኒስትሮች ሹመትና የዳኞችን ሹመት አፅድቋል።

በዚህም መሰረት ዶ/ር ቀነዓ ያዴታ የሃገር መከላከያ ሚኒስትር፣ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ዶ/ር ሳሙኤል ሁርቃቶ - የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትርና ፣ ኢንጅነር ታከለ ኡማ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትርነት ሹመት አፅድቋል።

የቀረበውንም ሹመት በአምስት ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ማፅደቁንም ምከር ቤቱ በፌስቡክ ገፁ አስፍሯል።

ከዚህም በተጨማሪ 40 የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞችን ሹመትና የ50 የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ሹመቶችንም በአብላጫ ድምፅ ማፅደቁን አስፍሯል። ተሿሚዎችም ቃለ መሃላቸውን መፈፀማቸውንም ሰፍሯል።