ኢትዯጵያ፡ አገራዊ ምርጫው በዚህ ዓመት መካሄድ እንደሚችል ተገለጸ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ስድስተኛው ዙር አገራዊ መርጫ ሊካሄድ እንደሚችል የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ አስታወቁ።

በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት አስከ አንድ ዓመት ለሚደርስ ጊዜ እንዲሸጋገር የተወሰነው ምርጫ እንዲካሄድ የወረርሽኙ ሁኔታን በተመለከተ ከጤና ባለስልጣናት የሚሰጡ ምክሮችን መሰረት እንደሚያደርግ ተገልጾ ነበር።

በዚህም መሰረት የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በአገሪቱ ያለውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሁኔታን በተመለከተ የመስሪያ ቤታቸውን ግምገማ ለሕዝብ ተወካዮች ምከክር ቤት ባቀረቡበት ጊዜ ነው አገራዊ ምርጫን ለማካሄድ እንደሚቻል አመልክተዋል።

ካለው የወረርሽኝ ስጋት አንጻር የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎችን ከግምት ውስጥ የሚያስገባ የምርጫ ሥነምግባር፣ ደንብና ማስፈፀሚያ መመሪያዎችን በማዘጋጀት ስድስተኛውን አጠቃላይ ምርጫ ማካሄድ እንደሚቻል ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

አክለውም ምርጫውን ለማካሄድ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት ካጋጠመ "ይህ በተለየ ሁኔታ መታየት ሊያስፈልገው እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀት ያስፈልጋል" ሲሉ ሚኒስትሯ በሪፖርታቸው ላይ ጠቅሰዋል።

ሚኒስትሯ እንዳሉት በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ወረርሽኙ በሁሉም ክልሎች የተሰራጨ ሲሆን፤ በዚህም የኮሮናቫይረስ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 95 በመቶ የሚሆኑት የታወቀ የጉዞ ታሪክ የሌላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

እስካሁንም በተደረገው ምርመራ ከ66 ሺህ 200 ሰዎች በላይ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን 1 ሺህ 45 ሰዎች በወረርሽኙ ምክንያት መሞታቸውን ገልጸዋል።

ነገር ግን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት እየቀነሰ ባይሆንም የቅድመ መከላከልና ስርጭቱን በመግታት ሂደት ውስጥ በሁሉም ደረጃ አቅም ማሳደግ መቻሉን አመልክተዋል።

በዚህም የአገሪቱ የመመርመርም ሆነ የክትትል አቅም በማደጉ በከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ጋር መድረስ እንደተቻለ ተናግረዋል።

ከዚህም ባሻገር ከበሽታው መከላከልና ሕክምና አንጻር የተሰሩ ሥራዎችንና የተገኙ ውጤቶችን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ለምክር ቤቱ ዝርዝር የሆነ ሪፖርት አቅርበዋል።

በአገሪቱ ካለው የወረርሽኝ መስፋፋት ሁኔታ አኳያ አገራዊ ምርጫን ከማካሄድ አንጻር የበርካታ አገራት ተሞክሮዎች ላይ ምልከታ የተደረገባቸው ሲሆን፣ በአንዳንዶቹ በወረርሽኝ ወቅት ምርጫ ተካሂዷል፤ በአብዛኞቹ ደግሞ እንዲተላለፍ ተደርጓል።

በኢትዮጵያም በሽታውን የመከላከልም ሆነ የመቆጣጠር ዝግጅነቱ ዝቅተኛ በነበረበት ወቅት ምርጫን ማከናወን ስጋቱ የበለጠ የሚያሳድገው በመሆኑ በተላለፈው ውሳኔ እንዲራዘም መደረጉ ይታወሳል።

ስለዚህም ወረርሽኙ የጤና ስጋት መሆኑ እንዳለ ቢሆንም ቀደም ሲል ከነበረው ልምድ እንፃር ከፍተኛ አለመሆኑ፣ በሽታው ከዚህም በኋላ ረዘም ላለ ጊዜ ስጋት ሆኖ ሊቆይ ሰለሚችል፤ ምርጫው ሲራዘም ከነበርንበት ሁኔታ አንጻር ስለስርጭቱ የተሻለ መረጃ መኖሩ ተገልጿል።

እንዲሁም አስፈላጊውን የበሽታው ምርመራ፣ ክትትል፣ ሕክምናና ጥንቃቄን በተመለከተ የተሻለ አቅምና ግንዛቤ በመኖሩ፤ በተጨማሪም የተለያዩ አገራትን የምርጫ ተሞክሮን በማየት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላት ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ እንዳለ ተገልጿል።

ይህንንም ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀጣዩን አገራዊ ምርጫን በተመለከተ በቀረበውን የጤና ሚኒስቴር ሪፖር ላይ በመወያየት ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው ምርጫ በኮሮናቫይረስ ስጋት ሳቢያ እንዲራዘምና በክልሎችና በፌደራል ደረጃ ያሉት ምክር ቤቶች ቀጣዩ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ በሥራቸው ላይ እንዲቀጥሉ መወሰኑ ይታወሳል።