ምርጫ ቦርድ ከትግራይ ክልል የቀረበለትን ጥያቄ እንዳልተቀበለው አስታወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ምርጫን እንዲያስፈፅምለት ያቀረበውን ጥያቄ ያልተቀበለው መሆኑን ገለጸ።

ቦርዱ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ወረርሽኙን እየተከላከለ ስድስተኛውን ዙር ምርጫ ለማካሄድ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በሚያዘው መሰረት ምርጫውን እንዲያስፈጽም የሚያስፈልገውን ዝግጅት እንዲያደርግና ውሳኔውን ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቅ መጠየቁን ገልጾ ነው ይህንን ምላሽ የሰጠው።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰጠው መልስ ላይ እንዳመለከተው በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማስፈፀም የሚያስፈልጉ እንቅስቃሴዎችን በማከናወን ላይ እያለ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው ወረርሽኝ በኢትዮጵያም በመከሰቱ ምርጫውን ለማስፈፀም ሲያካሂዳቸው የነበሩት ሥራዎች እንደተስተጓጎሉ ገልጿል።

በዚህም ምክንያት ያለውን ሁኔታ በመገምገምና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር በማድረግ አገራዊው ጠቅላላ ምርጫ ቀደም ሲል ቦርዱ ባወጣው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ማካሄድ የማይቻል በመሆኑ ይህንኑ ውሳኔ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ምክር ቤቱም የቀረበለትን የቦርዱን ውሳኔ ተቀብሎ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት መወሰኑ አስታውሷል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤትም በሰጠው ውሳኔ ምርጫውን ወረርሽኙ የሕዝብ ጤና ስጋት ሆኖ ባለበት ሁኔታ ማካሄድ የማይቻል በመሆኑ የፌደራልና ክልል ምክርቤቶች የስልጣን ዘመን እንዲቀጥል መወሰኑን እንዲሁም አጠቃላይ ምርጫው ወረርሽኙ የሕዝብ ጤና ስጋት አለመሆኑን ካረጋገጡበት ጀምሮ ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ አዓመት ባለው ጊዜ እንዲካሄድ መወሰኑን ገልጿል።

ቦርዱ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ላይ አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድበት ጊዜ እንዲራዘም ምክንያት የሆነው የወረርሽኝ ሁኔታ እንደገና ተገምግሞ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩ እስኪረጋገጥ ድረስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በየትኛውም የአገሪቱ ክልል ምርጫ አያካሄድም ሲል በመግለጫው አመልከልቷል።

ጨምሮም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፓለቲካ ፓርቲዎችን መመዝገብ፣ መቆጣጠር እና ማስተዳደር፣ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን ማውጣት፣ የምርጫውን ከተጽእኖ ነጻ እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ማስፈጸም ስልጣን ያለው ብቸኛ ተቋም መሆኑን ገልጾ ስለዚህም በኢትዮጵያ ውስጥ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳን፣ አፈጻጸምንም ሆነ ተያያዥ ሁኔታን የሚወስነውም ቦርዱ ብቻን እንደሆነ ገልጿል።

በመሆኑም የትግራይ ክልል ምክር ቤት በክልሉ ውስጥ ስተኛውን ዙር የክልል ምክር ቤት ምርጫ እንዲካሄድ ውሳኔ ለመስጠት እንዲሁም ቦርዱ ይህንን ውሳኔውን ተቀብሎ ሊያስፈጽም ይገባል የሚልበት ህጋዊ መሠረት የለውም ሲል ጥያቄውን እንዳልተቀበለው አስታውቋል።