ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ የኮሎምቢያው ነፃ አውጭ ጦር መሪን ላስያዘ 5 ሚሊዮን ዶላር እሸልማለሁ አለች
አሜሪካ የኮሎምቢያ ብሔራዊ ነፃ አውጭ ጦር (ናሽናል ሊበሬሽን አርሚ) መሪን ያለበትን ለጠቆመና ላስያዘ አምስት ሚሊዮን ዶላር ሽልማት አዘጋጅቻለሁ አለች።
የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ኃላፊ ማይክ ፖምፔዮ የነፃ አውጭ ጦሩ በምህፃረ ቃል ኢኤልኤን መሪ ዊልቨር ቪሌጋስን "በዕፅ የተወነጀለ አሸባሪ" በማለት በትዊተር ገፃቸው ወርፈውታል።
ማይክ ፖምፔዮ ኮሎምቢያን ከጎበኙ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው ይህንን ያሉት።
ምንም እንኳን ማይክ ፖምፔዮ ይህንን ይበሉ እንጂ ኢኤልኤ ከአምሳ አመት በፊት ኢፍትሃዊነትን ለመታገል የተመሰረተ የማርክሲስት ርዕዮተ አለምን የሚከተል ነፃ አውጭ ድርጅት ነኝ ይላል።
የነፃ አውጭው ጦር የአሁኑ መሪ የ38 አመቱ ዊልቨር ቪሌጋስ ፓላሚኖን ለባለፉት 20 አመታት ኮኬይን ከኮሎምቢያ ወደ አሜሪካ በማዘዋወር ኢኤልኤን ይደጉማል በማለት ወንጅለውታል።
ማይክ ፖምፔዮ በተጨማሪም የኮሎምቢያ መንግሥት "እነዚህን ወንጀለኛ ድርጅቶች ለመገርስስ በሚያደርገው ትግልም አሜሪካ ቀኝ እጅ ትሆናለች" ብለዋል።
ስለ ኢኤልኤን በጥቂቱ
- ኢኤልኤን የተመሰረተው በጎሮጎሳውያኑ 1964 ሲሆን በኮሎምቢያ ያለውን ኢ-ፍትሃዊ የመሬት ቁጥጥርን ለመገርሰስ ያለመ ነው። መሬት በሃብታሞችና በጥቂቶች እጅ መሆኗንም በፅኑ ተቃወመ፤ መነሳሻ የሆነው የ1959 የኩባ አብዮት እንደሆነም ይነገራል።
- በባለፉት አስርት አመታት መሬትን በቁጥጥራቸው ስር ያደረጉ ከበርቴዎችን፣ ትልልቅ ኩባንያዎችን ኢላማ አድርጓል።
- በገጠራማዋ ኮሎምቢያ ከፍተኛ ድጋፍ ያለው ሲሆን እንደነ አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት ሽብርተኛ ድርጅት ነው በማለትም በአደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪነት፣ ሰዎችን በማገት ይወነጅሉታል።
የኮሎምቢያ መንግሥት ድርጅቱን በአሸባሪነት የሚወነጅለው ሲሆን በ2016ም ጁዋን ማኑኤል ሳንቶስ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት ከሌላኛው የግራ ክንፍ ታጣቂ ፋርክ ጋር ስምምነት ቢፈጥሩም ከኢኤል ኤን ጋር ግን በጊዜ ይደር ትተውት ነበር።
በተለይም አዲሱ ፕሬዚዳንት ዱኬስ ከመጡ በኋላም ቡድኑ በዋና መዲናዋ ቦጎታ የሚገኝ የፖሊስ ማሰልጠኛ አካዳሚን በቦምብ በማፈንዳት፤ ለ21 ሰዎች ህልፈት ተጠያቂ አድርገውታል።
ከዚህም በተጨማሪ በደቡብ ናሪኖ ግዛት ለደረሱ ግድያዎችም ተጠያቂ መንግሥት ቢያደርገውም ኢኤልኤን ፍፁም ውንጀላ ነው በማለት ክዶታል።