'ዘ ሻዶው ኪንግ'ን ለመፃፍ አስር ፈታኝ አመታት እንደወሰደባት ደራሲ መዓዛ መንግሥቴ ትናገራለች

ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉ ሴት የነፃነት ታጋዮችን በሚዘክረው 'ዘ ሻዶው ኪንግ' መፅሃፏ ኢትዮጵያዊ-አሜሪካዊቷ ደራሲ መዓዛ መንግስቴ ለቡከር ሽልማት እጩዎች መካከል አንዷ ሆናለች።

ለነፃነት በተደረገው ትግል ላይ የጥቂት ወንዶች ሚና በጎላበት ሁኔታ ሴት ነፃነት ታጋዮች ከታሪክ መዝገብ መፋቃቸውንና ግዙፍ አስተዋፅኦቸው ምን ይመስል ነበር በማለት አስርት አመታትን ወደ ኋላ ተጉዛም መዓዛ በ'ዘ ሻዶው ኪንግ' ታስቃኛለች።

የፅሁፍ ስራው ግን ቀላል አልነበረም፤ መዓዛ እንደምትለው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች የተደራረቡበት ሁኔታም ነበር።

ጣልያንኛ መማር ነበረባት እንዲሁም የመጀመሪያ ረቂቅ ፅሁፉን ለማጠናቀቀም አሰልቺና አድካሚ የሚባሉ አምስት አመታት ፈጅተውባታል።

በመሰላቸት ፅሁፉን ጥላው እንደነበርም ለቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ሬድዮ ፕሮግራም ተናግራለች።

"በጣም ፈታኝና ከፃፍኩዋቸው ሁሉ መጥፎ የምለው ነው። እስርስር አድርጎኝ ነበር፤ የሞራል ውድቅትም ደርሶብኝ ነበር። የመጀመሪያ ረቂቄንም ጥዬ እንደገና ከዜሮ ጀምሬያለሁ" ብላለች።

መፅሃፏንም ፅፋ ለማጠናቀቅ አስር አመት ወስዶባታል።

ስለ ፅሁፍ ስታወራም " የፅሁፍ ስራ በደንብ ውስጥን መመልከትና መነሳሳትን ይጠይቃል። አንዳንዴ ወንበሬ ላይ ተቀምጬ መፃፍም ከፍተኛ ትግል ነበረው። ከመፅሃፌም ጋር አብሬ አድጌያለሁ። ለዚህ ሽልማትም ዕጩ በመሆኔ የተሰማኝ ፍፁም ደስታ ነው" ትላለች።

መጽሐፉ መቼቱን ያደረገው የሁለተኛው አለም ጦርነት ጅማሮ የሚባለውና ፋሽስት ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ነው።

"ስለ ጣልያኖች በተለምዶ የሚባሉ ነገሮችን ማካተት አልፈለፈግኩም፤ ስለዚህ ጣልያንኛ ተማርኩ። ጣልያኖችን አዋርቻለሁ። የወታደሮቹን ልጅና ልጅ ልጆችም እንዲሁ። በጦርነቱ ወቅት የመዘገቧቸውን ሁኔታዎች፣ ደብዳቤዎችና የግል መረጃዎችም በራሴ ፈትሻለሁ" ትላለች መዓዛ

"የቋንቋ ችሎታዬም ሲዳብር፣ ገፀ ባህርያቶቼም እየተወሳሰቡ መጡ" በማለትም ታስረዳለች።

በዩናይትድ ኪንግደም የፅሁፍ ዘርፍ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው የቡከር ሽልማት በእንግሊዝኛ ለተፃፉ ድርሰቶች ሽልማትን ይሰጣል።

በዩናይትድ ኪንግደም፣ አየርላንድ ለታተሙ ወይም ዬየትኛውም አገር ዜጎች ፅሁፋቸው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለሆኑ ነው።

ከመዓዛ መንግሥቴ በተጨማሪ የዚምባብዌዋ ፂፂ ዳንጋሬምባም 'ሞርነብል ቦዲ' በሚለው ድርሰቷ እጩ ሆናለች።

አሸናፊዎቹም ህዳር መጀመሪያው ሳምንት ላይ ለህዝብ ይፋ ይሆናሉ።