ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ካሜሮን፡ ሴቶችና ህፃናትን የገደሉ ወታደሮች በእስራት ተቀጡ
በካሜሮን ሁለት ሴቶችና ሁለት ህፃናትን የገደሉ ወታደሮች የአስር አመት እስር ተፈርዶባቸዋል። ግድያው የተፈፀመው ከአምስት አመታት በፊት ነው።
ከሁለት አመታት በፊት ግድያው ሲፈፀም የሚያሳይ ቪዲዮም ወጥቶም ብዙዎችን አስደንግጦ ነበር። ቪዲዮውም ላይ ፊታቸው ሴቶቹ ጭንቅላታቸው ሲሸፈንና ሲተኮስባቸው ያሳያል።
መጀመሪያ ላይ "ሃሰተኛ መረጃ" በሚል የካሜሮን መንግሥት ለማጣጣል ቢሞክርም በኋላ ግን ሰባት ወታደሮችን በቁጥጥር ስር አውሏል።
የቢቢሲው ምርመራ ዘጋቢ ፕሮግራም አፍሪካ አይ ባደረገውም ምርምር ጥቃቱ የደረሰው በሰሜናዊ ካሜሮን በምትገኝ መንደር መሆኑን ማረጋገጥ ችሏል።
የሶስቱን ተኳሽ ወታደሮችም ማንነት ማወቅም ተችሏል።
በተንቀሳቃሽ ምስሉ (ቪዲዮው) ላይ እንደሚታየው ወታደሮቹ ሴቶቹን ቦኮ ሃራም ትደግፋላችሁ በማለት ሲወነጅሏቸው ይታያል። ቦኮ ሃራም በናይጄሪያ የሚንቀሳቀስ ፅንፈኛ ታጣቂ ቡድን ሲሆን ናይጄሪያን በሚያዋስኗት ድንበር ከተሞችም ተስፋፍቷል ይባላል።
አንደኛዋ እናት ልጅ አዝላ የነበረ ሲሆን ወደ መገደያቸው ቦታም ወታደሮቹ ሲመሯቸው ያሳያል። በአቧራ በተሸፈነው መንገድ ከወሰዷቸው በኋላም ወደ ሆነ ስፍራ ወስደው አይናቸውን ሸፍነው 22 ጊዜም ተኩሰባቸዋል።
ከሰባቱ ወታደሮች አንደኛው በካሜሮና መዲና ያውንዴ በወታደራዊ ፍርድ ቤት ቀርቦ የነበረ ሲሆን ነፃ ወጥቷል ተብሏል።
ከሱ በተጨማሪ አንደኛው ወታደርም ነፃ የወጣ ሲሆን አራቱ ወታደሮች ግን በግድያው በነበራቸው ሚና እያንዳንዳቸው አስር አመት ተፈርዶባቸዋል።
ሌላኛው ወታደርም ሲገደሉ ቪዲዮ በመቅረፁና ለተለያዩ ሚዲያዎች በማጋራቱ የሁለት አመት እስር ተበይኖበታል።
የቢቢሲ ምርመራ ዘገባ ሁኔታውን ማጋለጡ ተከትሎ በርካታ ሚሊዮኖች ያዩት ሲሆን በአለም አቀፍ ደረጃም ሁኔታው እንዲጋለጥ አድርጎታል።