ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡በእንግሊዝ የለይቶ ማቆያን መመሪያ የጣሱ ሰዎች 13 ሺህ ዶላር ይቀጣሉ ተባለ
ራሳቸውን ለይተው እንዲቆዩ የተነገራቸው እንግሊዛውያን መመሪያውን ካላከበሩ 13 ሺህ ዶላር እንደሚቀጡ መንግሥታቸው ከሰሞኑ አስታውቋል።
በአዲሱ መመሪያ መሰረት የኮሮናቫይረስ ተመርምረው ፖዘቲቭ መሆናቸው ከተረጋገጠ ወይንም በኮሮናቫይረስ ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ግንኙነት መኖራቸው የታወቀ ሰዎች ራሳቸውን ለይተው እንዲቆዩ የሚያዝ መመሪያ ወጥቷል።
በአገሪቷ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንደገና ማገርሸቱን ተከትሎም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠበቅ ያለ መመሪያ እንዲወጣ ያዘዙት።
በትናንትናው ዕለት፣ መስከረም 9፣ 2013 ዓ.ም 4 ሺህ 422 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 27 ግለሰቦችም ህይወታቸው አልፏል።
ከዚህም በተጨማሪ በስኮትላንድ 350 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተዘገበ ሲሆን፣ ከግንቦት ወር በኋላም ከፍተኛ ነው ተብሏል። በዌልስ 212 ና በሰሜን አየርላንድ 222 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተገልጿል።
መመሪያውን ለተላለፉ በመጀመሪያ 1 ሺህ 300 ዶላር የሚያስቀጣ ሲሆን በተደጋጋሚ መመሪያውን ለሚጥሱት እስከ 13 ሺህ ዶላር ያስቀጣል።
ከዚህም በተጨማሪ ጥሰቱ ከፍተኛም መሆኑ ከተረጋገጠ በመጀመሪያም ቢሆን መመሪያውን ለሚጥሱ 13 ሺህ ዶላር ቅጣት ይጠብቃቸዋል።
በእንግሊዝ እስካሁን ድረስ ግለሰቦች ራሳቸውን እንዲያገሉ የምክር አገልግሎት ብቻ ነበር የሚሰጣቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አዲሱን መመሪያ ባወጁበት እለትም ቫይረሱን ለመታገል ሁሉም መመሪያውን ማክበር አለበት ብለዋል።
"ሁሉም ቢሆን ይሄ አዲሱ መመሪያ ጠቃሚ እንደሆነ ሊረዳ ይገባል። መመሪያውን ሁሉም ሊያከብረው ይገባል። የብሄራዊ ጤና አገልግሎት በሚያዛችሁ መሰረት ቫይረሱ ተገኝቶባችሁም ከሆነ በቫይረሱ ከተያዘ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ካላችሁ ራሳችሁን ለይታችሁ ልታቆዩ ይገባል። ካለበለዚያ ግን እነዚህን መመሪያዎች ተላልፋችሁ ከተገኛችሁ ጠበቅ ያለ ቅጣት ይጠብቃችኋል" በማለት ተናግረዋል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ስርጭት ለመግታት እንዲሁም ተጋላጭ ማህበረሰቦቹን ከቫይረሱ ለመታደግና ህይወት ማዳንም እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክር ቢጤ አዘል መልእክታቸውንም አስተላልፈዋል።
እስካሁን ድረስ 19 ሺህ ሰዎች መመሪያውን የጣሱ ሲሆን ከግማሽ በላይ የሚሆኑትም የተጣለባቸውን ቅጣት እንዳልከፈሉም ከጠቅላይ አቃቤ ህግ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
ከዚህም በተጨማሪ አቅማቸው ደካማ ለሆኑ ሰዎች በአንድ ጊዜ የሚሰጥም 650 ዶላር ይኖራል ተብሏል።