የጀርመን እግር ኳስ ቡድን በኮሮና ፍርሃት 37 ለ 0 ተሸነፈ

የእግር ኳስ ሜዳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቅርጫት ኳስ ውጤት አይደለም፡፡ የእግር ኳስ ነው፡፡ አንድ የጀርመን እግር ኳስ ቡድን በባለጋራው 37 ለ 0 ተሸንፏል፡፡

‹ለመሆኑ ተጫዋቾቹ ሜዳ ላይ ነበሩ ወይ?› ብሎ መጠየቅ የአባት ነው፡፡ አዎ ነበሩ፡፡

ነገር ግን በኮሮና ምክንያት 7 ተጫዋችችን ብቻ ነበር ለማሰለፍ የተገደዱት፡፡ 7ቱ ተጫዋቾችም ቢሆኑ የኮቪድን ማኅበራዊ መራራቅ ሕግን አጥብቀው ለማክበር ሲሉ አይጠጋጉም ነበር፡፡

ኳስ በርቀት እየመቱ መናበብ አቃታቸው፡፡ ይህ 37 ጎሎች የገቡበት ቡድን ሪፕዶርፍ ይባላል፡፡ ሪፕዶርፍ በእሁዱ ግጥሚያ ማሰለፍ የቻለው በእግር ኳስ ጨዋታ ማሰለፍ የሚቻለውን ትንሽ ቁጥር ነው፡፡ 7 ተጫዋቾች ብቻ፡፡

ይህን ያደረገው 4 ተጫዋቾች በጉዳት ቀርተው ወይም ቀይ ካርድ አይተው አይደለም፡፡ ኮሮናን ለመከላከል በሚል ነው 7 ተጫዋች ብቻ ያሰለፈው፡፡ ሪፕዶርፎች በዚህ ደረጃ ኮሮናን ለምን ፈሩ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

ቡድኑ የበዛ ጥንቃቄ ያደርግ የነበረው ተጋጣሚው ኤስ ቪ ሆልደንስቴድ ቀደም ባለ ጨዋታ፣ አንድ ተጫዋቹ በኮቪድ መያዙ ከተሰማ በኋላ ነው፡፡ በዚህ ግጥሚያ ግን ሁሉም ተጫዋቾች ኮሮና እንደሌለባቸው ቢረጋገጥም ተሸናፊው ቡድን ግን እርግጠኛ ስላልሆነ ነው ጎዶሎ ተጨዋቾችን በማሰለፍ ከቫይረሱ ለመጠበቅ የሞከረው፡፡

ከዚህ ይልቅ ጨዋታውን ለምን ፎርፌ አልሰጡም ሊባል ይችላል፡፡ ሪፕዶርፍ ያን ቀን በጨዋታው ባይገኝ 200 ፓውንድ ቅጣት ይጠብቀው ነበር፡፡

200 ፓውንድ ከየት ይመጣል? ቡድኑ ይህን ዓይነት ታሪካዊ ሽንፈት ከመሸነፉ ቀደም ብሎ ጨዋታው እንዲሰረዝለት ቢጠይቅም ውድድሩን የሚያስተናብረው የአካባቢው የስፖርት ማኅበር ግን ጥያቄውን ውድቅ አድርጎበት ነው ለዚህ ውድቀት የዳረገው፡፡

ሪፕዶርፍ የኳስ ቡድን አባላት እንደተናገሩት ባለፈው ጊዜ በኮቪድ ታመመ የተባለው የባለጋራው ቡድን ተጫዋች ፍርሃት ውስጥ ከቷቸዋል፡፡

ምክንያቱም ከሱ ጋር ንክኪ የነበራቸው ልጆች በዚህ ጨዋታ ተሰልፈው ሊሆን ይችላል በሚል ተጠግቶ ኳስ ለመቀማት የሚሞክር አልነበረም፡፡

ነገር ግን ሁሉም የባለጋራ ተጨዋቾች ተመርምረው ከቫይረሱ ነጻ ተብለው ነው የተሰለፉት፡፡

‹ተመርምረው ነጻ ተብለው የለም ወይ? ለምን ፈራችሁ ሲባሉ›› ቢመረመሩም የነሱ ተጨዋች በኮሮና መያዙ ከተነገረ 14 ቀናት አላለፈውም ነበር፤ ስለዚህ ራሳችንን መጠበቅ ነበረብን ብለዋል፡፡

የአሸናፊው ቡድን ሆልደንስቴት አሰልጣኝ ፍሎሪያን ሺዋተር በበኩላቸው ይህንን ጨዋታ ባልተጨበጠ ፍርሃት ተመስርቶ መሰረዝ አግባብ አይደለም፤ ስለዚህ ባገኘነው ክፍተት ተጠቅመን በሰፊ የጎል ልዩነት ማሸነፍ ችለናል ብለዋል፡፡

39 ጎል የገባበት ቡድን 90 ደቂቃውን ሙሉ ይጫወት አይጫወት ዘገባው ያለው ነገር የለም፡፡

ኮሮና
Banner