ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ካናዳ፡ በሰዓት 150 ኪሎ ሜትር እየነዳ እንቅልፍ የጣለው ካናዳዊ ተቀጣ
ካናዳዊው ሰው የሚያሽከረክረው ዘመናዊውን ቴስላ መኪና ነው፡፡ መኪናው ያለ ሾፌር እርዳታ አንድን ሰው ከቦታ ቦታ የሚወስድ ነው፡፡
መኪናው በሰዓት 150 ኪሎ ሜትር እየከነፈ ሾፌሩ ግን እንቅልፉን ይለጥጥ ነበር፡፡
ፖሊስ እንደሚለው መኪናው ክንፍ አውጥቶ በዚያ ፍጥነት ሲበር የሾፌሩ ወንበር ወደ ኋላ ተለጥጦ ከወንበር ይልቅ አልጋ ይመስል ነበር፡፡
መኪና ዘዋሪውም ይሁን አብሮት አጠገቡ የነበረው ተሳፋሪ ወንበራቸውን ዘርግተው ተኝተው ነበር፡፡
አልበርታ አካባቢ ሲደርሱ ነው የነቁት፡፡
ኤስ የተሰኘው የቴስላ ቅንጡና ዘመነኛ መኪና 140 ኪሎ ሜትር በሰዓት ራሱን ያስኬዳል፡፡ ፖሊስ የነቃው መኪናው 150 በሰዓት መብረር ሲጀምር ነው፡፡
የ20 ዓመቱ የመኪናው አሽከርካሪ ጎረምሳ፣ ፍርድ ቤት ለታኅሣሥ ቀጥሮታል፡፡
የጎረምሳው አሽከርካሪ ክስ ከተፈቀደ ፍጥነት በላይ ማሽከርከር ሆኖ ለ24 ሰዓት መንጃ ፍቃዱ የተነጠቀ ሲሆን፣ ቀጥሎ ደግሞ በአደገኛ አነዳድ ክስ ተመስርቶበታል፡፡
ተመሳሳይ ክስተት በሐምሌ ወር ፖኖካ አካባቢ ደቡብ ኤድመንተን አጋጥሞ ነበር፡፡
ሳጅን ዳሪ ተርንበል ለካናዳው ሲቢሲ ዜና እንደተናገሩት መኪናው በዚያ ፍጥነት ሲምዘገዘግ ማንም ሰው ስፖኪዮም ይሁን የፊት መስታወቱን የሚመለከት አልነበረም፡፡ ይህም አስደንጋጭ ነው፡፡
ሳጅን ጨምረው እንዳሉት መኪናውን መከታተል ሲጀምሩ ፍጥነት እየጨመረ መጣ፡፡ ምክንያቱም ከፊቱ መንገዱ ክፍት መሆኑን ሲያይ መኪናው በራሱ ጊዜ ፍጥነት ይጨምር ነበር፡፡ ማንም ግን ይህን የሚከታተል አሽከርካሪ አልነበረም፡፡ አሽከርካሪው ተኝቶ ነበር፡፡
23 ዓመታት በትራፊክ ፖሊስነት ሰርቻለሁ ያሉት ሳጅን ዳሪ እንዲህ ዓይነት ጉድ አይቼም ሰምቼም አላውቅም ብለዋል፡፡
በእርግጥ ሳጅን እንደዚያ ይበሉ እንጂ እሳቸው ትራፊክ ፖሊስ በነበሩባቸው ዓመታት ራሱን በራሱ የሚዘውር ዘመነኛ መኪና አልተፈጠረም ነበር፡፡
ቴስላ መኪናዎች አሁን ደረጃ-2 በሚባል ሁኔታ ነው የሚነዱት፡፡ ይህም ማለት መኪናዎቹ ራሳቸውን በራሳቸው ቢዘውሩም፤ ሾፌር መሪ ሳይጨብጥ የቅርብ ክትትል ሊያደርግላቸው ግዴታ አለበት፡፡
የቴስላ መኪናዎች ፈጣሪ ኤለን መስክ በዚህ ዓመት ያለ ምንም ሾፌር እርዳታ መኪናዎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲዘውሩ ይጠብቃል፡፡
ያን ጊዜ ምናልባት ሾፌሮች እየነዱ እንቅልፋቸውን መለጠጥ ይችሉ ይሆናል፡፡