ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ ፡ ከአንዲት ዶክተር በስተቀር ሁሉም ዶክተሮች የተሰደዱባት ከተማ
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የመን ሲገባ በከተማዋ አደን አገልግሎት የሚሰጠው ሆስፒታል አንድ ብቻ ነበር። በአደን ከተማ ከአንድ ሚሊየን በላይ ሰዎች እንደሚኖሩ ይገመታል።
ታዲያ በዚህ ወቅት በሽታውን በመፍራትና የሕክምና ግብዓቶች ባለመኖራቸው አብዛኞቹ ዶክተሮች ከተማዋን ጥለው ወጥተዋል።
በዚህ ጊዜ በከተማዋ የኮቪድ-19 ታማሚዎችን ለማከም በፈቃዷ የቀረችው ዶክተር ዞሃ ብቻ ናት።
በጦርነት በፈራረሰችውና ምንም በሚባል ደረጃ በሥራ ላይ ያለ ሆስፒታል በሌላት ከተማ፤ የወረርሽኙ ስርጭት ሲጨመር ምን ልትሆን እንደምትችል ማሰብ ቀላል ነው።
እዚህ ላይ የአብዱልከሪም ያለፈበትን ፈተና እናንሳ።
አብዱልከሪም አሊ የዚህችው ከተማ ነዋሪ ነው። ታዲያ አንድ ቀን አባቱ አሊ በጠና ታመሙበት።
ሰውነታቸው እየደከመ መምጣቱን ተመለከተ። ለክፉ የማይሰጣቸው ቀላል ጉንፋን ያዳከማቸው ነበር የመሰለው።
ከዚያ ግን እየባሰባቸው ሲመጣ ወደ ሆስፒታል ይዟቸው ሄደ። ያን ጊዜ ሌሎች ጥቂት ሆስፒታሎች ነበሩ። ራጅ ከተነሱ በኋላ አባቱ የደረት ኢንፌክሽን እንዳጋጠማቸው ተነገረው።
በወቅቱ ፅኑ ሕሙማን ክፍል መግባት ያስፈልጋቸው ነበር።
ይሁን እንጂ ዶክተሮቹ ሆስፒታሉ እንደዚህ ዓይነት የጤና እክሎችን እንዳማይስተናግድ ገልጸው፤ ኮሮናቫይረስ ሊኖርባቸው ይችላል በሚል አባቱ በሆስፒታሉ መቆየት እንደማይችሉ አረዱት።
አብዱልከሪም አባቱን ይዞ አምስት ሆስፒታሎችን አዳረሰ። ግን ቫይረሱን በመፍራትና የበሽታ መከላከያ የሕክምና ግብዓት ስለሌለ የትኛውም ሆስፒታል ተቀብሎ ሊያክምለት አልቻለም።
በዚህም ሳቢያ አብዛኞቹ ዶክተሮች ጥለው በመሰደዳቸው ከአንድ ሆስፒታል በስተቀር አብዛኞቹ ሆስፒታሎች ዝግ ነበሩ።
በሆስፒታሉ የኮቪድ-19 ታማሚዎችን ለማከም ፈቃደኛ የሆነች ብቸኛዋ ዶክተር ዞሃ ነበረች።
አብዱልከሪም ዶ/ር ዞሃን ያገኛት ለአንድ ሳምንት ያህል ሲያፈላልጋት ቆይቶ ነው።
ዶ/ር ዞሃ፤ አብዱልከሪም ሲያገኛት "አባቴ ሊሞት ነው! እባክሽ!" እያለ እንደተማፀናት ትናገራለች።
እርሷም አልጋም ሆነ ኦክስጅን እንደሌለ ነገረችው። በእርግጥ አባቱ ተጎድተው ነበር፤ ለመተንፈስም ይቸገሩ ነበር።
አብዱልከሪም "አባቴ ሊሞት ነው. . . እባክሽ ዶክተር" እያለ በተማጽኖ ከመጮህ በዘለለ ሌላ የሚያደርገው ነገር አጣ።
ዶ/ር ዞሃም ሁኔታውን አይታ ምንም የምትረዳቸው ነገር ባይኖርም አባቱ ሆስፒታሉ እንዲገቡ አደረገች። ያለውን የኦክስጅን ጭምብል አጠለቁላቸው።
ይሁን እንጅ ሊተርፉ አልቻሉም። ሆስፒታል ከገቡ ከ15 ደቂቃ በኋላ ሕይወታቸው አለፈ።
የየመን መንግሥት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመዋጋት ምንም ያደረገው ቅድመ ዝግጅት አልነበረም።
በሁለት የጦርነት ግንባሮች አጣብቂኝ ውስጥ ነበር ያለው።
በሰሜን ለስድስት ዓመታት በዘለቀው ከሁቲ አመፂያን ጋር የሚያደርገው ፍልሚያ፤ በሌላ በኩል አደንን ለመቆጣጠር በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከሚደገፈው ኃይል ጋር የሚያደርገው ጦርነት።
በዚህም ሳቢያ ኮሮናቫይረስ በአገሪቱ ሲሰራጭ ጉዳቱን የከፋ አድርጎታል።
አንድ በከተማዋ የሚገኝ የመቃብር ቆፋሪም እንዲህ ዓይነት ነገር ገጥሞት እንደማያውቅ ተናግሯል። "ከጦርነት በላይ አስከፊ ነው" ሲል ነበር ሁኔታውን የገለጸው።
መቃብር ቆፋሪው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመግባቱ በፊት በአማካይ በቀን 10 ሰዎችን ነበር የሚቀብረው።
"አስክሬን ወደ እኛ ይመጣል፤ ነገር ግን እንደ አሁኑ አይደለም" ብሏል። በአንድ ወር ውስጥ 1 ሺህ 500 አስክሬን እንደቀበረ በመግለጽ።
ወሩን ሙሉ ዶክተር ዞሃ ካለችበት ሆስፒታል መግባት የቻሉ ሰዎች ፍፃሜም ይኽው ነበር።
አሁን ግን ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በአካባቢው ገብተዋል።
"ቡድኑ ከመድረሱ በፊት እያንዳንዱ ታማሚ ከሆስፒታሉ የሚወጣው አስክሬኑ ነበር። አሁን አንዳንዶቹ ታማሚዎች አገግመው በእግራቸው መውጣት ችለዋል" ትላለች ዶ/ር ዞሃ። ልዩነቱም የገሃነምና የገነት ያህል እንደሆነ በመግለጽ።