ኮሮናቫይረስ፡ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ተቋርጦ የነበረውን የክትባት ሙከራ ሊጀምር ነው

ዓለምን ላሽመደመደው ኮቪድ-19 ክትባት ለማግኘት ሁሉም በየአቅሙ ላይ ታች እያለ ነው።

ከእነዚህ መካከልም አስትራዜኒካ እና ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ እያበለፀጉ ያሉት ክትባት ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎበታል።

ለዚህም ነው ማክሰኞ ዕለት የክትባት ሙከራው ለጊዜውም ቢሆን መሰናከሉ ሲሰማ በበርካቶች ዘንድ ድንጋጤን የፈጠረው።

ትናንት ግን የተመናመነውን ተስፋ መልሶ የሚያለመልም ዜና ተሰምቷል።

ይሄው አስትራዜኔካና በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ እየሰሩት ያለው ዓለም ተስፋ የጣለበት የኮቪድ-19 ክትባት ሙከራ ሊጀመር መሆኑ ተገልጿል።

የክትባት ሙከራው እንዲቆም የተደረገው በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኙ አንድ የሙከራው ተሳታፊ ላይ የጎንዮሽ ችግር በመታየቱ ነበር።

ባሳለፍነው ማክሰኞም አስትራዜኔካ፤ ምርምሩ እንዲቆም የተደረገው በሙከራው ተሳታፊ ላይ የታየው የጤና ችግር ከክትባቱ ጋር ይያያዝ፤ አይያያዝ እንደሆነ ለመፈተሽ እንደሆነ ተናግሯል።

ይሁን እንጅ ቅዳሜ ዕለት ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የክትባቱን ሙከራ መቀጠል እንደሚቻል አስታውቋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የጤና ሴክሬታሪ ማት ሃንኮክ ሙከራው እንደገና ሊቀጥል የመሆን ዜናውን በደስታ ተቀብለዋል።

"ሙከራው እንዲቆም መደረጉ የሚያሳየው፤ ለደህንነት ቅድሚያ እንደምንሰጥ ነው። ተመራማሪዎቻችን በአፋጣኝና በተቻለ መጠን ውጤታማ የሆነ ክትባት እንዲያቀርቡም እንደግፋቸዋለን" ብለዋል።

ዩኒቨርስቲው በበኩሉ "ልክ እንደዚህ ሰፊ የክሊኒካል ሙከራዎች በሚደረጉበት ጊዜ አንዳንድ የሙከራው ተሳታፊዎች ጤናቸው ሊታወክ ስለሚችል፤ ሙከራው ለጊዜው እንዲቆም መደረጉ የሚጠበቅ ነው" ብሏል በመግለጫው።

ደህንነትን የሚመለከት ገለልተኛ ኮሚቴ እና የዩናይትድ ኪንግደም የመድሃኒትና እና የጤና መጠበቂያ ምርቶች ተቆጣጣሪ የሰጠውን ምክረ ሃሳብ ተከትሎም ምርምሩ አሁን ሊቀጥል እንደሚችልም አክሏል።

የምርምሩ ተሳታፊ ያጋጠማቸውን የጤና እክል በተመለከተ ሚስጢር ለመጠበቅ ሲባል እንደማይገልፅ የተናገረ ቢሆንም፤ ኒው ዮርክ ታይምስ በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙት የሙከራው በጎፈቃደኛው በአንድ በኩል ያለው የአከርካሬ አጥንታቸው ላይ ያሉ ነርቮች መቆጣት እንዳጋጠማቸው ዘግቧል።

በመላው ዓለም 180 የሚጠጉ የከትባት ሙከራዎች እየተካሄዱ ሲሆን እስካሁን ግን የክሊኒካል ሙከራቸውን አለማጠናቀቃቸውን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

ይህ ክትባት የመጀመሪያ እና ሁለተኛ የሙከራ ምዕራፉን በስኬት በማጠናቀቁ መጀመሪያ ላይ ገበያ ላይ ሊውሉ ይችላሉ ተብሎ ከፍተኛ ተስፋ ከተጣለባቸው ክትባቶች አንዱ ነው።

ክትባቱ ወደ ሦስተኛው የሙከራ ምዕራፍ የተሸጋገረው በቅርብ ሳምንታት ሲሆን 30 ሺህ በጎ ፈቃደኞችን አሳትፏል። እነዚህ በጎ ፈቃደኞች በአሜሪካ፣ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በብራዚል፣ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ናቸው።

በክትባት ማበልፀግ ሂደት ሦስተኛው ምዕራፍ በሺዎች የሚቆጠሩ በጎፈቃደኞች የሚሳተፉበት ሲሆን ዓመታትንም ሊወስድ ይችላል።

የአገሪቷ መንግሥት የሳይንስ አማካሪ ፓትሪክ ቫላንስ፤ ሙከራው የመቋረጡ ዜና በተሰማ ማግስት "በኦክስፎርድ የሙከራ ሂደት ላይ ያጋጠመው ያልተለመደ አይደለም" ብለዋል።