ሊሞት የተቃረበ አባታቸውን ሊሰናበቱ የፈለጉ አራት ልጆች ለለይቶ ማቆያ 600 ሺህ ብር ክፈሉ ተባሉ

በአውስትራሊያ በህይወትና በሞት መካከል ያለ አባታቸውን ሊሰናበቱ ከሌላ ከተማ ሊመጡ የፈለጉ አራት ልጆች ለሚያርፉበት ለይቶ ማቆያ ሆቴል አስራ ስድስት ሺህ ዶላር (600 ሺህ ብር) መክፈል አለባችሁ ተብለዋል።

የ39 አመት አባታቸው በካንሰር ህመም በፀና የታመመ ሲሆን ኩዊንስላንድ በምትባለው ከተማ ቤቱ ውስጥ ይገኛል። አራቱ ልጆቹ ደግሞ በሌላኛዋ ከተማ ሲድኒ ናቸው ያሉት።

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት አውስትራሊያ ከከተማ ወደ ከተማ የሚደረግ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ የጣለች ሲሆን የኩዊንስላንድ ባለስልጣናትም ለዚህ ሲሉ ህጉን እንዲያላሉት ብዙዎች ተማፅነዋቸዋል።

ሁኔታው ቁጣን በመቀስቀሱም ከ200 ሺህ ዶላር በላይም ገንዘብ ተዋጥቷል።

መጀመሪያ ላይ ህመምተኛው ማርክ ኪንስ አንድ ልጅ ብቻ ሊያየው እንደሚችልና ከልጆቹም መምረጥ እንዳለበት ተነግሮት ነበር።

በኋላም የግዛቲቷ አስተዳደር ሁኔታውን አሻሽለው ሁሉም ልጆቹ መጥተው እንዲያዩትና እንዲሰናበቱት ፈቀዱ።

ሆኖም ልጆቹ ለሁለት ሳምንታት ያህል በራሳቸው ወጪ በሆቴል ለይቶ ማቆያ እንዲገቡም እንደ ቅድመ ሁኔታ ተቀመጠላቸው።

ከዚህም በተጨማሪም ልጆቹ አባታቸውን በሚጎበኙበት ወቅት ሰውነታቸው በሙሉ በመከላከያ መሸፈን አለበት።

"ባለቤቴ እሱን ለማየት ይህን ያህል ክፍያ ክፈሉ እያላችሁን ነው? ለመቅበርስ ምን ያህል ሊያስወጣን ነው? አለችኝ" በማለት የልጆቹ አያት ብሩስ ላንግቦርን ለ7 ኒውስ ተናግረዋል።

ልጆቹን አባታቸውን እንዲያዩና እንዲሰናበቱም ለማስቻል በጎ ፈንድ ሚ ገንዘብ እየተሰባሰበ ነው።

መጀመሪያ ታቅዶ የነበረው 30 ሺህ ዶላር ለመሰብሰብ ቢሆንም ባልተጠበቀ ሁኔታም 200 ሺህ ዶላር ተዋጥቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰንም አንድ ሺህ ዶላር አዋጥተዋል።

በገንዘብ ማሰባሰቢያው ድረገፅም በርካቶች ቤተሰቦቹን ያፅናኑ ሲሆን፤ የኩዊንስላንድ አስተዳደርም ከፍተኛ ትችትን እያስተናገደ ነው።

በርካቶችም "ሊሞት የተቃረበ አባታቸውን እንዳያዩ እንዴት ይከለከላሉ? እንዲህ አይነት ገንዘብ ክፈሉ ማለትም አሳፋሪና ጨካኝነት ነው"ብለውታል።

የኩዊንስላንድ የጤና ኃላፊዎች በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት አለም አቀፍ ወረርሽኝ እየታገሉ ከመሆናቸው አንፃር ህዝቡን በተለይ ተጋላጭ ማህበረሰቡን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አስምረዋል።