ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
2012፡ ከጃዋር መሐመድ እስከ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም፡ የ2012 አይረሴ ንግግሮች።
2012 ዓ. ም. ኢትዮጵያ እንደተቀረው ዓለም ሁሉ በኮሮናቫይረስ የተፈተነችበት፣ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች የተቀሰቀሱበት፣ ብሔራዊ ቤተ መንግሥቱ ለሕዝብ ክፍት የሆነበት፣ ትግራይ ክልላዊ ምርጫ ያካሄደበትም ነበር።
ባሳለፍነው ዓመት ከነበሩ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ የምጣኔ ሀብት፣ የስፖርትና ሌሎችም ሁነቶች ጋር በተያያዘ እነማን ምን አሉ? በዓመቱ ጎልተው ከወጡ ንግግሮች መካከል ዐሥሩን መርጠናል።
የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ ኮሮናቫይረስን በተመለከተ ያደረጉት ንግግር ነው። በርካታ አገራት የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ጥለው ነበር። ኢትዮጵያ ግን ይህን ማድረግ የሚያስችል የምጣኔ ሀብት አቅም እንደሌላት ጠቅላይ ሚንስትሩ መናገራቸው ይታወሳል።
2012 ላይ በቁጥጥር ስር ከዋሉ ታዋቂ ፖለቲከኞች መካከል አቶ ጃዋር መሐመድ ይገኝበታል። አቶ ጀዋር የተቀላቀሉት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ብሔራዊ ፓርቲ (አብፓ) ጋር በጥምረት ለመሥራት ስምምነት ላይ ደርሰው እንደነበርም ይታወሳል።
ውሳኔው በፖለቲካው ጎልተው ከወጡ ጉዳዮች አንዱ ነበር። ይህን ተከትሎም ቢቢሲ ከአቶ ጀዋር መሐመድ ጋር ባደረገው ቆይታ "አገር ትፈረካከሳለች ብዬ እፈራ ነበር" ማለቱ አይረሳም።
አትሌት ሲፈን ሃሰን የዓለም ሻምፒዮንሺፕ ባለድል ከሆነች በኋላ ቢቢሲ ቃለ መጠይቅ አድርጎላት ነበር ። "የምፈራው አትሌት የለም። ማሸነፍ እንጂ ለቅጽበትም ቢሆን መሸነፍን አላስብም" የምለው አትሌቷ፤ በወቅቱ የሰጠችን ምላሽ መነጋገሪያ ሆኖም ነበር።
አገራዊው ምርጫ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ቢሰረዝም በትግራይ ክልላዊ ምርጫ ተካሂዷል። ህወሓት በአብላጫ ድምጽ ማሸነፉም ተገልጿል። ክልሉ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከፌደራል መንግሥት ጋር አንድ ሁለት ሲባባል ዓመቱ ተገባዷል።
ምክትል ፕሬዘዳንቱ በአንድ ወቅት "ትግራይ ላይ ያለው ጥላቻ ካልተስተካከለ፤ ትግራይ ራስዋን የቻለች አገር ትሆናለች" ማለታቸው አይዘነጋም።
ቢቢሲ ይህንን ንግግር ተመርኩዞ የሠራውን ዘገባ ማስፈንጠሪያውን በመጫን ማንበብ ይችላሉ።
የዓለም ጤና ድርጅትን የሚመሩት ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም የመላው ዓለም መገናኛ ብዙሀን ሰፊ ሽፋን ሲሰጧቸው ከከረሙ ግለሰቦች አንዱ ናቸው። ከወራት በፊት ዘረኛ ጥቃቶች እየተሰነዘሩባቸው እንደሆነና እሳቸው ግን ኃላፊነታቸውን ከመወጣት ምንም እንደማያግዳቸው ተናግረው ነበር።
በመቀሌ ከተማ ማርያም ሰባ የተሰኘ የሚታጠብ የሴቶች የንፅህና መጠበቂያን በማምረት ሥራ ላይ የተሰማራቸው ፍረወይኒ መብራህቱ አምና መነጋገሪያ ከነበሩ አንዷ ናት። ሲኤንኤን የዓመቱ ምርጥ ብሎ ሽልማት ሲያበረክትላት፤ እንደ ነውር የሚታየው የወር አበባ ክብር ማግኘቱን ተናግራ ነበር።
ቢቢሲ ስለ ፍረወይኒ ተሞክሮ የሠራውን ዘለግ ያለ ዘገባ ማስፈንጠሪያውን ተጭነው ያገኛሉ።
በቅርቡ ከተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፣ አካል ጎድሏል፣ ንብረትም ወድሟል። ንብረታቸውን ካጡ ሰዎች መካከል አንዱ ዝነኛው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ አንዱ ነው። አትሌቱ "ሞትም ቢመጣ እዚሁ ነው የምጋፈጠው ሲል" ምንም ነገር ቢፈጠር ከመሥራት ወደኋላ እንደማይል አስረግጦ ተናግሮ ነበር።
ቢቢሲ "እሷ ማናት" በሚል አምድ በተለያየ ዘርፍ ላይ የተሠማሩ በርካታ ሴቶችን አስተናግዶ ነበር። ስለ ሕይወት ተሞክሯቸው፣ ስለገጠሟቸው መሰናክሎችም ተናግረዋል። የመብት ተሟጋችና ጠበቃ ሐበን ግርማ በተደረገላት ቃለ መጠይቅ የአካል ጉዳት ህልሟን ከማሳካት እንዳላገዳት ገልጻ ነበር።
ሐበን ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቆይታ ያደረገችው ንግግር በ2012 ከሚታወሱት መካከል ይጠቀሳል።
ታላቁ ቤተ መንግሥት ታድሶ ለሕዝብ ክፍት መደረጉ አምና ከተከሰቱ ነገሮች መካከል አንዱ ነው። በቤተ መንግሥቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የእድሳት እና የአረንጓዴ መናፈሻውን ሥራ ከሚሠሩት ባለሙያዎች መካከል አንትሮፖሎጂስቷ መስከረም አሰግድና የሥነ ጥበብ ባለሙያው ኤሊያስ ስሜ የሚመራው ቡድን ይጠቀሳል።
መስከረም ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቆይታ "መንግሥት ቤተ መንግሥት የሕዝብ ነው ብሎ ለመክፈት ማሰቡ ትልቅ ነገር ነው" ብላ ነበር።
የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ህልፈት በዓመቱ አሳዛኝ ከነበሩ ክስተቶች ዋነኛው ነው። አንጋፋው ድምጻዊ አሊ ቢራ ስለ ሃጫሉ የተናገረውን ነገር በርካቶች ተጋርተውት ነበር። ከአሊ ጋር ቢቢሲ ያደረገውን ቆይታ ማስፈንጠሪያውን ተጭነው ያገኛሉ።