ኮሮናቫይረስ ፡ ክትባቱን ቀድሞ የሚያገኘው ማን ይሆን? እንዴትስ ይከፋፈላል?

ተመራማሪዎች ለኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ የሚሆን ክትባት ማግኘት ሲችሉ በፍጥነት ለመላው ዓለም በሚበቃ መልኩ ማዘጋጀት አዳጋች ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም።

የምርምር ላብራቶሪዎችና ትልልቅ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ከዚህ በፊት አንድን ክትባት ለማዘጋጀት፣ ለመፈተሽ፣ ለማምረትና ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ የሚወስደውን ጊዜ በመሻር በፍጥነት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

ክትባቱ በእርግጠኝነት ሲገኝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማከፋፈልም የሚደረገው ጥረት እንደቀጠለ ነው። ነገር ግን በሀብታም አገራት መካከል ክትባቱን ለማግኘት በሚደረገው እሽቅድድም ተጋላጭ የሆኑት የዓለማችን ማኅበረሰቦቸ ተጎጂ ይሆናሉ።

ክትባቱን ማነው ቀድሞ የሚያገኘው? ምን ያህል ያስወጣ ይሆን? የእንቅስቃሴ ገደቦች ተጥለው በሚገኙበት በዚህ ወቅት ክትባቱን እንዴት በፍጥነት በሁሉም ቦታ ማዳረስ ይቻላል? የሚሉት ወሳኝ ጥያቄዎች አልተመለሱም።

ከዚህ ቀደም በነበረው ተሞክሮ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ጥቅም ላይ የሚውሉ ክትባቶችን ለማዘጋጀት፣ ለመሞከርና ለማሰራጨት ዓመታትን ይወስድ ነበር። እንደዚያም ሆኖ ክትባቶች ስኬታማ የማይሆኑበት አጋጣሚዎች አሉ።

የሰው ልጅ የፈንጣጣ በሽታን ከምድረ-ገጽ ለማጥፋት 200 ዓመታት ወስዶበታል።

ምንም እንኳን ክትባት ቢገኝላቸውም እንደ ፖሊዮ፣ ቲታነስ፣ ቲቢ እና የመሳሰሉ በሽታዎች ደግሞ አሁንም ድረስ አብረውን ይኖራሉ።

ክትባቱ መቼ ዝግጁ መሆን ይችላል?

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያሳትፉ የሙከራ ሥራዎች በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም በሚገኙ የምርምር ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በደህናው ዘመን ከአምስት እስከ አስር ዓመታት ይወስድ የነበረው ፍቱን ክትባት የማግኘቱ ሥራ አዋጪ እንደማይሆን የተገነዘቡት አንዳንድ አገራት፤ ደርሰንበታል ያሉት የክትባት አይነትን በብዛት ለማምረት በዝግጅት ላይ ናቸው።

አምራቾችም ለክትባቱ የሚረዳ በቢሊየኖች የሚቆጠር ዶላር ፈሰስ ለማድረግ ተዘጋጅተው እየጠበቁ ነው።

ባሳለፍነው ወር ደግሞ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የኮቪድ-19 ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፍቃድ ማግኘቱን ተናግረው ነበር።

በአገራቸው ላለፉት ሁለት ወራት በሰዎች ላይ ሙከራ እየተደረገበት የነበረው ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል መፈቀዱን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።

ክትባቱ አስፈላጊውን የምርመራ ሂደት ማለፉን የገለጹት ፑቲን፤ ልጃቸው ክትባቱን እየወሰደች እንደምትገኝም ተናግረዋል።

ጥቅምት ወይም ኅዳር ላይ ክትባቱን በጅምላ የመስጠት እቅድ እንዳለ የአገሪቱ አመራሮች ቢናገሩም፤ ባለሙያዎች የሩሲያ የክትባት ምርምር እየሄደ ያለበት ፍጥነት ላይ ጥያቄ አንስቷል።

የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ ሩሲያ ክትባት ስታመርት ዓለም አቀፍ ሕግጋትን እንድትከተል ማሳሰቡም አይዘነጋም።

የሩሲያ ክትባት ድርጅቱ በሦስተኛ ደረጃ ሙከራ ላይ ይገኛሉ ብሎ ከዘረዘራቸው ክትባቶች መካከል አደይለም። እነዚህ ክትባቶች በሰዎች ላይ ተሞክረው ተጨማሪ ምርምር መካሄድ አለበት።

ፕሬዘዳንት ፑቲን ግን፤ በሞስኮው ጋማሊያ ተቋም ውስጥ የተሠራው ክትባት ቫይረሱን “በዘላቂነት ለመከላከል የሚያስችል” ነው ብለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ቃል አቀባይ ክርስቲያን ሊንድሜር "አንዳንዴ በግላቸው ምርምር የሚያካሂዱ ሰዎች ውጤታም እንደሆኑ ይናገራሉ። ይህም እጅግ መልካም ዜና ነው" ብለዋል።

ቃል አቀባዩ አያይዘውም፤ ውጤታማ ክትባት በማግኘት እና በምርምር ደረጃዎች በማለፍ መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለም አስምረውበታል።

በመላው ዓለም ክትባቱን ለማግኘት ሙከራ በማድረግ ላይ የሚገኙት ቀሪዎቹ ተቋማት ደግሞ ክትባታቸው በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት ፈቃድ እንደሚገኝ ተስፋ አድርገዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ግን እስከ ፈረንጆቹ 2021 አጋማሽ ድረስ በርከት ያሉ ለኮቪድ-19 የሚሆኑ ክትባቶችን ላንመለከት እንችላለን ሲል ተደምጧል።

የእንግሊዙ ግዙፍ የመድኃኒት አምራች ኩባንያ አስትራዜኔካ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እየበለጸገ የሚገኘውን ክትባት ለማምረት ፈቃድ ያገኘ ሲሆን ለዩናይትድ ኪንግደም 100 ሚሊየን የክትባት ብልቃጦችን ለማምረት ተስማምቷል። ለተቀረው ዓለም ደግሞ 2 ቢሊየን የክትባት ብልቃጦችን አምርቶ ለማከፋፈል አቅሙ እንዳለው አስታውቋል።

ፋይዘር እና ባዮንቴክ የተባሉት ሌሎች ግዙፍ ኩባንያዎች ደግሞ ለኮቪድ-19 ክትባት ለማግኘት እስካሁን ድረስ 1 ቢሊየን ዶላር ወጪ ማድረጋቸውን በመግለጽ በያዝነው ዓመት የፈረንጆቹ ጥቅምት ወር ላይ የማምረት ፈቃድ እንደሚያገኙ ተስፋ አድርገዋል።

ፈቃድ የሚያገኙ ከሆነ ደግሞ የፈረንጆቹ 2020 ከማለቁ በፊት ቢያንስ 100 ሚሊየን የክትባት ብልቃጦችን እንዲሁም ከዚያ በኋላ ደግሞ በ2021 ተጨማሪ 1.3 ቢሊየን ብልቃጦችን ማምረት አለባቸው።

ከእነዚህ ትልልቅ ድርጅቶች በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ 20 የሚሆኑ መድኃኒት አምራቾች ክሊኒካል ሙከራቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ።

ነገር ግን ሁሉም ስኬታማ እንደማይሆኑ ይታወቃል፤ ብዙ ጊዜ ክትባት ለመስራት ላይ ታች ከሚሉት ድርጅቶች መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው ተሳክቶላቸው ማምረት የሚጀምሩት።

የክትባት ፖለቲካ

የእንግሊዙ አስትራዜኒካ በቅልጥፍና ያመርተዋል የተባለው ይህ የኮሮናቫይረስ ክትባት መድኃኒት በዋናነት እንዲደርስ የታሰበው ደግሞ መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው አገሮች ነው።

አስትራዜኒካ በበኩሉ ለፍጥነት እንዲረዳው ከሌሎች ሁለት ኩባንያዎች ጋር ስምምነት አድርጓል። ከእነዚህ መካከል የመጀመሪያው የሕህንዱ ሴሩም ኢንዲያ አንዱ ሲሆን፤ ይህ መድኃኒት አምራች በዓለም ላይ መድኃኒትን በከፍተኛ መጠን በማምረት አቅሙ ተስተካካይ የለውም።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ባስተላለፉት መልዕክት ''እየጠበቅን ያለው ክትባት ለሁሉም የሰው ልጆች በእኩል የሚደርስ የሕዝብ ክትባትን ነው'' ካሉ በኋላ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በየአቅሙ ርብርብ እንዲያደርግም ተማጽነዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ለጊዜው ስማቸው ካልተጠቀስ ስድስት መድኃኒት አምራቾች ጋር ስምምነት መፈረሙ ተሰምቷል። አሜሪካም ብትሆን እስከ ጥር ወር ባለው ጊዜ ውስጥ 300 ሚሊየን የክትባት ብልቃጦችን ለማግኘት እየሰራች ነው።

ነገር ግን ሁሉም የዓለማችን አገራት በዚህ ፍጥነት ክትባቶቹን ማግኘት አይችሉም።

ከዚህ ቀደም ከትባቶችን በማከፋፈል የሚታወቁት እንደ 'ሜድሲንስ ሳንስ ፍሮንቲርስ' ያሉ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ደግሞ አገራት ከመድኃኒት አምራች ድርጅቶቹ ጋር የሚያደርጉት ድርድር የክትባት ፉክክር እንዳይፈጥር ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

በዚህም ድርጅቶቹ የሚያመርቱትን ክትባት በሙሉ ሃብታም አገራት የሚቀራመቱት ከሆነ ደሃዎቹ አገራት ሊዘነጉ ነው ማለት ነው።

ከዚህ በፊት በነበሩ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት የሕይወት አድን ክትባቶች ስርጭት ጉዳይ በርካታ አገራት ህጻናትን ከተላላፊ በሽታዎች መከላከል እንዳይችሉና ለሚሊየኖች ሞት ምክንያት ሆኗል።

አንዲት ብልቃጥ ክትባት ምን ያክል ይጠየቅባት ይሆን?

በአሁኑ ጊዜ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ክትባት ለማግኘት እና ለማምረት ፈሰስ እየተደረገ ነው።

ለዚህም ወጪውን ከሞላ ጎደል እየሸፈኑ የሚገኙት ባለጸጋ አገራት ናቸው። እያደጉ ያሉ አገራት ክትባቱን በርካሽም ሆነ በነጻ ለማግኘት ድርድር ላይ ናቸው።

የክትባቶች ዋጋ አገራት በሚያዙት መጠን ላይ የተመሰረተ ነው።

ለምሳሌ ሞደርና የተባለው መድኃኒት አምራች ኩባንያ ለኮቪድ-19 ይሆናል ያለውን ክትባት በብልቃጥ ከ32 እስከ 37 ዶላር ድረስ እንደሚሸጥ ገልጿል።

አስትራዜኒካ ደግሞ ክትባቱን ባመረተበት ዋጋ እንደሚሸጠው አልያም እጅግ በጣም በረከሰ ዋጋ እንደሚያከፋፍለው አስቃውቋል።

በሕንድ የሚገኘው በዓለማችን ትልቁ የክትባት አምራች ኩባንያ ሴረም ኢንስቲትዩት ደግሞ ከጋቪ እና ከቢልና ሜሊንዳ ፋውንዴሽን የ150 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ያገኘ ሲሆን እስከ 100 ሚሊየን ክትባቶችን ለዝቅተኛ ገቢ አገራት ለማቅረብ ተስማምቷል።

የዓለም ጤና ድርጅት፣ ዩኒሴፍ እና ሌሎች ድርጅቶች ክትባቱ ከተገኘ በአግባቡ ማሰራጨት የሚያስችል ሥርዓት ቀደም ብለው ዘርግተዋል። ማቀዝቀዣ ያላቸው መኪኖች፣ በፀሐይ የሚሰሩ ማቀዝቀዣዎች እና ማከማቻ መጋዘኖች ከዚህ በፊት ለነበሩ ክትባቶች ጥቅም ላይ ሲውሉ ነበር።

እነዚሁ መገልገያዎችም ለኮሮናቫይረስ ክትባት ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ይጠበቃል።