ሞ ፋራህ በኃይሌ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን አሻሸለ

ትውልደ ሶማሊያዊው ሞ ፋራህ በኃይሌ ገብረስላሴ ለ13 ዓመታት ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን አሻሸለ።

ለግሬት ብሪቴን የሚሮጠው የአራት ጊዜ የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ሞ ፋራህ የአንድ ሰዓት የዓለም ክብረ ወሰንን በዳይመንድ ሊግ ውድድር ነው ትናንት ምሽት ማሻሻል የቻለው።

ፋራህ በአንድ ሰዓት ውስጥ 23.33 ኪሎ ሜትር በመሮጥ ነው የሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴን 21.285 ኪሎ ሜትር ርቀት ያሻሻለው።

“የዓለም ክብረ ወሰንን መስበር ቀላል ነገር አይደለም። ይህን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። ይህ ክብረ ወሰን ለረዥም ጊዜ ሳይሰበር ቆይቷል” ሲል ከውድድሩ በኋላ ሞ ፋራህ ተናግሯል።

በዚህ ውድድር አትሌቶች በአንድ ሰዓት ውስጥ በተቻላቸው መጠን ረዥም ርቀትን ለመሸፈን ይወዳደራሉ።

ከዛ ቀደም ብሎ በተካሄደ ተመሳሳይ የሴቶች ውድድርም ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሲፈን ሃሰን በተመሳሳይ የዓለም ክብረ ወሰንን ማሻሻል ችላለች።

ለኔዘርላንድ የምትሮጠው ሲፈን ያሻሻለችው ክብረ ወሰን በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ድሬ ቱኔ ተይዞ የነበረውን ነው።

ሲፈን በአንድ ሰዓት ውስጥ 18.930 ኪሎ ሜትር በመሮጥ ከ14 ዓመታት በፊት ድሬ ቱኔ አስመዝግባ የነበረውን 18.517 ኪሎ ሜትር ማሻሻል ችላለች።