ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቤይሩት፡ በህንፃዎች ፍርስራሾች ውስጥ በህይወት ያሉ ሰዎችን ማግኘት ተስፋ የመነመነ ነው ተባለ
በባለፈው ወር በሊባኖሷ መዲና ቤይሩት በደረሰው ፍንዳታ ተቀብረው በሚገኙ ህንፃዎች ፍርስራሾች ውስጥ ሰዎችን ለማዳን ጥረቱ ቢቀጥልም "በህይወት ይገኛሉ" የሚለው ተስፋ የመነመነ እንደሆነ ተገልጿል።
ከሰሞኑ በሚደረገው ፍለጋና ህይወት የማትረፍ ስራ በአንደኛው መሳሪያ የሰው ልብ ምት ከህንፃው ፍርስራሽ ውስጥ ቢሰማም፤ ፍርስራሹን ከተነሳ በኋላ ግን ምንም ነገር አልተገኘም።
በቦታውም ከቺሊ የመጡ ቡድኖችን ጨምሮ አምሳ በጎ ፈቃደኞች ተገኝተዋል።
ቤይሩትን ባንቀጠቀጣት ፍንዳታ 190 ሰዎች ሲሞቱ በርካታ ሺዎች ቆስለዋል።
ጌምዛያነ ማርና ሚክሃኤል ተብለው በሚጠሩ የመኖሪያ ስፍራዎች በሚገኙ ቦታዎችም ነዋሪዎች ዘመዶቻቸው በህይወት እንዲገኙ ተአምር እየጠበቁ ተሰባስበውም ታይተዋል።
ከቺሊ የመጣው የአዳኞች ቡድን በአካባቢው ሲዘዋወሩ ውሻው በህይወት ያለ ሰው እንዳለ ምልክት በዚህ ሳምንት ረቡዕ ሰጠ ይህንንም ተግባር በተከታዩ ቀንም ደገመው።
መሳሪያም አምጥተው ሲመረምሩ በተመሳሳይ መልኩ የልብ ምት ሰጣቸው። የልብ ምቱም ጥልቀቱ ሶስት ሜትር ፍርስራሽ ውስጥ ነው እንዳለ ነው የተገመተው።
የህንፃውን ፍርስራሽ በመሳሪያ በመታገዝ እንዲሁም በእጃቸው ቢያነሱትም እስካሁን የህይወት ፍንጭ አላገኙም።
በትናንትናው ዕለትም በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ የቺሊ በጎ ፈቃደኞች አዳኝ ቡድን ኃላፊ ፍራንሲስኮ ሌርማንዳ እንዳሉት "እስካሁን በህይወት ያለ ሰው ምልክት እንኳን አላገኘንም" ብለዋል።
ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በባለፉት ሁለት ቀናት የተመዘገቡት እስትንፋሶች ከህንፃው ስር የሚሰሩ በጎ ፈቃደኞች ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በሕይወት የሚገኙ ሰዎችን ፍለጋ የሚለው አስከሬናቸውና ቀሪ አካላቸውን መፈለግ ወደሚል እንደሚዞርም አስረድተዋል።
ሆኖም" አንድ በመቶ ቅንጣት ተስፋ ካለችም አናቆምም፤ ቀሪ አካላቸውን እየፈለግን እነሱንም በህይወት የሚገኙ ከሆነ እንፈልጋለን" ብለዋል።
የቺሊው አዳኝ ቡድን በጎርጎሳውያኑ 2010፣ 700 ሜትር ጥልቀት ባለው ማዕድን ማውጫ ተቀብረው የነበሩ 33 ማዕድን አውጭዎችን በሁለት ወራት ፍለጋ በማዳንም ይታወቃል።
የሊባኖስ ባለስልጣናት እንዳሳወቁት በፍንዳታው ሰባት ሰዎች መጥፋታቸውን ነው። በዚህ ሳምንት አርብም በፍንዳታው ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የህሊና ፀሎት ተደርጓል።