ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቤይሩት ፍንዳታ፡ የሊባኖስ መንግሥት ሥልጣን ለቀቀ
ባለፈው ማክሰኞ በዋና ከተማዋ ቤይሩት ውስጥ ከደረሰው ፍንዳታ ጋር በተያያዘ የሊባኖስ መንግሥት በገዛ ፈቃዱ ሥልጣን ለቋል።
ከ200 በላይ ሰዎች ለሞት የተዳረጉበት በሊባኖስ ቤይሩት በሚገኝ ወደብ ላይ የደረሰው ፍንዳታን ተከትሎ ፀረ-መንግሥት ተቃውሞዎች ተፋፍመው ነበር።
ሰኞ አመሻሽ ላይ ነው ገዢው የሊባኖስ መንግሥት ሥልጣን መልቀቁን በቴሌቪዥን መስኮት ያሳወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃሰን ዲያብ ናቸው።
በርካታ ሊባኖሳዊያን ለፍንዳታው የገዢው ፓርቲ አመራሮችን ይወቅሳሉ፤ በሙስና ተጠምደው ረስተውናልም ይላሉ።
ቤይሩትን ያናወጠው ፍንዳታ የተከሰተው 2750 ቶን የሚመዝን አሞኒዬም ናይትሬት የተባለ ንጥረ ነገር ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ ለበርካታ ዓመታት በመከማቸቱ ነው።
ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በደረሰው ፍንዳታ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 220 መድረሱንና 110 ሰዎች ደግሞ የገቡበት እንደማይታወቅ የቤይሩት ከተማ ከንቲባ ማርዋን አቡድ አል-ማርሳድ ለተሰኘው የዜና ምንጭ ተናግረዋል።
በርካታ የውጭ አገር ዜጎችና የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች የገቡበት ካልታወቁ ሰዎች መካከል ናቸው ብለዋል ከንቲባው።
በፍንዳታው ሳቢያ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች ቤት አልባ ሆነዋል፤ የቀሩትም በርና መስኮቶቻቸውም ከጥቅም ውጪ ሆነዋል።
ፍንዳታውን ተከትሎ ፀረ-መንግሥት ተቃውሞ ሰልፈኞች የቤይሩትን መንገዶች አጨናንቀዋል፤ ፖሊስም ሰልፈኞቹን በአስለቃሽ ጭስ ለመበተን ሞክሯል።
ሊባኖሳዊያን በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ላይ ያላቸውን ቅሬታ ሲያሰሙ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። ፀረ-መንግሥት ተቃውሞዎች ለዓመታት የዘለቁ ናቸው።
አገሪቱ በምጣኔ ሃብት ድቀት መመታቷ ሳያንስ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ኑሮ መቀዛቀዙ ለሊባኖሳዊያን ፈተና ሆኗል።
ነገር ግን የዕለተ ማክሰኞው ፍንዳታ ብዙዎች ጣታቸውን መንግሥት ላይ እንዲቀስሩና ለተቃውሞ ወደ አደባባይ እንዲወጡ አድርጓቸዋል።
አሁን ያለው የሊባኖስ መንግሥት ባለፈው ዓመት በአገሪቱ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ሥልጣን የለቀቀውን መንግሥት ተከትሎ ወንበር የጨበጠ ነበር።