የሌባኖሷ ቤይሩት በከፍተኛ ፍንዳታ ተናወጠች

የቀድሞ የሌባኖስ ጠቅላይ ሚንስትር ራፊክ ሃሪሪ ላይ ግድያ ፈጽመዋል የተባሉ ግለሰቦች ላይ የፊታችን ዓርብ ብይን ለመስጠት የተዘጋጀችው የሌባኖስ መዲና ቤይሩት በከፍተኛ ፍንዳታ መናወጧ ተነገረ።

እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ፍንዳታው የተሰማው የከተማዋ ወደብ የሚገኝበት አቅራቢያ ነው። ምንም እንኳ እስካሁን ማረጋገጫ ባይገኝም ሁለተኛ ፍንዳታ መሰማቱም ተነግሯል።

ሁለተኛው ፍንዳታ ያጋጠመው በራፊክ መኖሪያ ቤት አቅራቢያ መሆኑን እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።

ለፍንዳታው ምክንያቱ ምን እንደሆነ እስካሁን የተገለፀ ነገር የለም።

ፍንዳታው ከተሰማ በኋላ ኢንተርኔት ላይ የተጫኑ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ህንጻዎችን እና ጭስ አስመልክተዋል።

ሆስፒታሎች ጉዳት ባጋጠማቸው ሰዎች ተጨናንቀዋል ተብሏል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል በበኩሉ የዓይን እማኞቹ ከፍርስራሽ ሥር የ10 ሰዎች አስክሬን ሲወጣ መመልከታቸውን ዘግቧል።

እአአ 2005 ላይ የቀድሞ የሌባኖስ ጠቅላይ ሚንስትር ራፊክ ሃሪሪን ገድለዋል የተባሉ አራት ተጠርጣሪዎች ላይ የፊታችን ዓርብ በሌሉበት ብይን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በጠቅላይ ሚንስትሩ ግድያ የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸው አራቱም ግለሰቦች በኢራን መንግሥት የሚደገፈው የሄዝቦላ ቡድን አባላት ናቸው።

ሄዝቦላ በጠቅላይ ሚንስትሩ ግድያ እጄ የለበትም ሲል በተደጋጋሚ ተከላክሏል።

የሌባኖስ ጠቅላይ ሚንስትር ሃማድ ሃሰን በፍንዳታው በርካቶች ላይ ጉዳት መድረሱን እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማጋጠሙን ተናግረዋል።

የሌባኖስ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ፍርስራሽ ሥር የወደቁ ሰዎች ምስልን አስመልክተዋል።

ይህ ፍንዳታ የተከሰተው የሌባኖስ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት ነው። የዓለም ምጣኔ ሃብት ፎረም በዓለማችን ላይ በከፍተኛ ውዝፍ እዳ ውስጥ ከሚገኙ አገራት መካከል ሌባኖስን በሦስተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል።

ከሳምንታት በፊት ሥራ አጥ የሆኑ የሌባኖስ ወጣቶች አደባባይ ወጥተዋል። የቫይረሱን ስርጭትም የአገሪቱን ኢኮኖሚ ግን 'ከድጥ ወደ ማጡ' እንዲገባ ሊያደርገው እንደሚችል ተገምቷል።