ኮሮናቫይረስ፡ ዶ/ር ፋውቺ ለክትባት መጣደፉ ቢቀርብን ይሻላል አሉ

ዶ/ር ፋውቺ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካ ዕውቅ የማኅበረሰብ ጤናና የተላላፊ በሽታዎች ጉዳይ ኃላፊ ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ ‹‹እኔ ተናግሪያለሁ! ይሄ ለክትባት የምንጣደፈው ነገር አላማረኝም›› እያሉ ነው፡፡

ይህን የተናገሩት ዶናልድ ትራምፕ የመጪው ምርጫ በለስ እንዲቀናቸው በሙከራ ላይ ያለን ክትባት ያለጊዜው ወደ ሕዝብ በማውጣት ‹ክትባት ደርሷልና ተከተቡ› እንዳይሉ ስጋት መፈጠሩን ተከትሎ ነው፡፡

ዶ/ር ፋውቺ በአሜሪካ ህዝብ ከትራምፕ የበለጠ ተሰሚነትና የመታመን ፀጋን ያገኙ ጎምቱ የጤና ባለሞያ ናቸው፡፡

ከሮይተርስ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት አንድን ክትባት የሕክምና ደንብና መርሆችን ሳይከተሉ ወደ ሕዝብ ማውጣት የሌሎች ክትባቶችን ተስፋ ያጨልማል፡፡

ትራምፕ አንድን ክትባት ሙሉ ሒደቱን ሳይጨርስና በብዙ ሰዎች ላይ ሙከራ ሳይደረግበት ይፋ ለማድረግ እየተዘጋጁ ነው የሚሉ መረጃዎች እየወጡ የሚገኙት ካለፈው ሳምንት ወዲህ ነው፡፡

ፕሬዝዳንቱ ይህን ለማድረግ የተበረታቱት በሕዝብ ዘንድ ያላቸውን ቅቡልነት በኅዳር ከሚደረገው ምርጫ በፊት ለመጨመር በመሻት ነው፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ትራምፕ ከጆ ባይደን ያነሰ ቅቡልና እንዳላቸው የሕዝብ ፖለቲካዊ ሙቀት መመተሪያ ዳሰሳ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡

ዲሞክራቶች ‹‹እኚህ ትራምፕ የሚባሉ ሰውዬ ለዝናቸው ሲሉ የአሜሪካውያንን ሕይወት ለፖለቲካ ቁማር እያዋሉት ይገኛሉ›› ብለው ከሰዋቸዋል፡፡

ባለፈው ቅዳሜ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትዊተር ሰሌዳቸው እንደጻፉት ከሆነ የአሜሪካ የምግብና የመድኃኒት አስተዳደር ለመድኃኒት አምራቾች ሥራቸውን እያደናቀፈባቸው ነው፡፡

ፕሬዝዳንቱ ይህን የሚሉት የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ‹ክትባት አምራቾች ትክክለኛውን የመድኃኒት አመራረት ሒደት ተከትለው እንዲሄዱ› በተደጋጋሚ በማሳሰቡ ነው፡፡

ፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ ዶናልድ ትራምፕ በኦክስፎድና በአስትራዜኔካ አማካኝነት እየተሞከረ ያለው ክትባት ለአስቸኳይ የሕክምና አገልግሎት በአቋራጭ ለሕዝብ እንዲቀርብ የሚቻልበትን መንገድ እየፈለጉ እንደሆነ ዘግቦ ነበር፡፡

እነ ኦክስፎርድ እየሞከሩት ባለው ክትባት ለመሳተፍ 10 ሺ አሜሪካዊያን ፈቃደኝነታቸውን አሳይተዋል፡፡

ነገር ግን የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን 30ሺህ ፈቃደኞች ካልተሟሉ ይሁንታን አልሰጥም እያለ ነው፡፡

የኦክስፎርድ ክትባት አሁን ዓለም ላይ እየተሞከሩ ካሉ በዐሥራዎቹ ከሚገኙ ምርምሮች እጅግ ተስፋ የተጣለበት ነው፡፡ ባለፉት ሳምንታት ታዋቂ መድኃኒት ፋብሪካዎች መድኃኒቶቻቸውን በመሞከር ላይ ተጠምደው ቆይተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የኤሜሪካ የምግብና መድኃኒት አስተዳደር የወባ መድኃኒት የሆነው ሀይድሮክሲክሎሮኪዩን ለኮሮና ታማሚዎች ቢሰጥ እንደማይቃወም ተናግሮ ነበር፡፡

ከዚያ በኋላ ግን መድኃኒቱ ከጥቅሙ ጉዳት ማመዘኑ በምርመራ በመረጋገጡ እውቅና ነፍጎታል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ይህን መድኃኒት ለሳምንታት መውሰዳቸውንና ፍቱን እንደሆነ እንደደረሱበት በተደጋጋሚ ይናገራሉ፡፡

ዶ/ር ፋውቺ እንደሚሉት ክትባቶች ትክክለኛውን አካሄድ ካልተከተሉ አደጋ ማስከተላቸው ብቻም ሳይሆን ሰዎች በቀጣይ በሚወጡ መድኃኒቶች እምነት ያጣሉ፣ እንዲመከርባቸው የሚፈቅዱ በጎ ፈቃደኞችንም ማሸሽ ይሆናል፡፡

ዶ/ር ፋውቺ ፖለቲካ ሕክምና ውስጥ ገብቶ መፈትፈት የለበትም፡፡ ሕክምና የራሱን መንገድ እንዲከተል ሊተው ይገባል የሚል አቋም አላቸው፡፡

ኮሮና
Banner