ጃዋር መሐመድ፡ ፍርድ ቤቱ የእነ አቶ ጃዋርን የባንክ ሒሳብ አለማገዱን ተናገረ

ጃዋር ሞሐመድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በትናንት ቀጠሮው በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ ቅድመ ምርመራ መዝገብ የዐቃቤ ሕግን የቃል ምስክር ሰምቷል።

ከዚህ ውጪ ደግሞ ባለፈው ቀጠሮ በተጠርጣሪዎች እንዲሁም ደግሞ በዐቃቤ ሕግ ለተነሱ አቤቱታዎች ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ከዚያ ውስጥ አንዱ አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ ከዚህ በፊት ሚዲያዎች ከእኛ ፈቃድ ውጪ ፎቶ እያነሱን ነው እንዲሁም ቪዲዮ እየቀረፁን ነው ይህ እንዲቆም ትዕዛዝ ይሰጥልን ሲሉ ጥያቄ አቅርበው ነበር።

ፍርድ ቤቱም በዚህ ጉዳይ ላይ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ይህ ጉዳይ የተጠርጣሪዎችን ነጻ ሆኖ፣ የመታየት መብት የሚጋፋ ነው። ስለዚህም ሚዲያዎች የችሎቱን የዕለት ውሎ ከመዘገብ ውጪ ያለተጠርጣሪዎች ፈቃድ ፎቶ ማንሳትም ሆነ ቪዲዮ መቅረጽ እንደማይችሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በሌላ በኩል ችሎት ውስጥ በብዛት እየታዩ እና እየታደሙ ያሉት የፌደራል ፖሊስ አባላት ናቸው፤ ስለዚህ ቤተሰቦቻችን ገብተው እንዲታደሙ ፈቃድ ይሰጠን ሲሉ ባለፈው ቀጠሮ ላይ አቤቱታ አቅርበው ነበር።

ፍርድ ቤቱም ፖሊሶቹ በብዛት የሚገኙት ለደኅንነትና ለጥበቃ እንደሆነ በመግለጽ ከአራት ያልበለጡ የተጠርጣሪዎች ቤተሰቦች ችሎቱን እንዲታደሙ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በሌላ በኩል የኦኤምኤን ጋዜጠኛ የሆነው ጋዜጠኛ መለሰ ድሪብሳ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ለፍርድ ቤቱ ቤተሰቦቹን በስልክ ማግኘት እንዲችል ያቀረበው አቤቱታ ላይ ውሳኔ ሰጥቷል።

መለሰ ድሪብሳ፤ ሌሎች ተጠርጣሪዎች በስልክ ቤተሰቦቻቸውን እንዲያገኙ እየተፈቀደላቸው ነው። ይሁንና እኛ ግን ከሌሎች በተለየ መልኩ ቤተሰቦቻችንን በስልክ እንዳናገኝ ተደርገናል ሲል አቤቱታውን አቅርቦ ነበር።

ፍርድ ቤቱም በትናንት ውሎው ጋዜጠኛ መለሰ ድሪብሳ ቤተሰቦቹን በስልክ ማግኘት እንዲችል ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ሌላው በትናንትናው ችሎት የተነሳው ጠበቆች ያነሱት የስልክ ጉዳይ ነበር።

የተጠርጣሪ ጠበቆች ባለፈው ችሎት ላይ ዐቃቤ ሕጎች ስልክ ይዘው እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል። እኛ ግን እየተከለከልን ነው። ስለዚህ ሁለታችንም እንከልከል አልያም ሁለታችንም ይፈቀድልን ሲሉ አቤቱታቸውን አሰምተው ነበር።

ችሎቱም ሁለቱም አካላት ወደ ችሎቱ ስልክ ይዘው መግባት እንደማይችሉ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

አቶ ጃዋር መሐመድ በትናንትናው ዕለት ያቀረቡት አቤቱታ ሲራጅ የሚባሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተለያዩ አካባቢዎች ንብረታቸው እንዲታገድ መደረጉን በተመለከተ ነው።

በተለይም የምዕራብ ሐረርጌ የተለያዩ ወረዳዎች ስም በመጥቀስ እንዲሁም ደግሞ አርሲ ውስጥ ባለሐብቶች በጃዋር ገንዘብ ነው የምትነግዱት በመባል ንብረታቸው እየታገደ እና እየተቀሙ እንደሆነ ይህም እንዲቆም ለፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን አቅርበዋል።

አቶ ጃዋር አክለውም የቤተሰባቸውም ሆነ የእርሳቸው የባንክ ሒሳብ ታግዶ እንደሚገኝ በመግለጽ ፖሊስ ምርመራውን ስለጨረሰ ይህ እግድ ወይንም ትዕዛዝ ይነሳልን ሲሉ ችሎቱን ጠይቀዋል።

ችሎቱም ፍርድ ቤቱ የአቶ ጃዋርንም ሆነ የቤተሰባቸውን የባንክ ሂሳብ እንዳላገደ ገልጾ፤ ያገደውን አካል መጠየቅ እንደሚችሉ ተነግሯቸዋል።

አቶ በቀለ ገርባ በበኩላቸው በሚዲያዎች ከፍተኛ የሆነ ዘመቻ እየተካሄደብን ነው። "ይህም መንግሥት ምርጫ ላይ እንዳንሳተፍ ወይንም ደግሞ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምርጫ ላይ እንዳይሳተፉ እየተጠቀመበት ያለ ዘዴ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

"ይህ በሚዲያዎች የሚደረግብን ዘመቻ በእኛም ሆነ በቤተሰቦቻችን ህይወት ላይ አደጋን ጥሏል። ስለዚህ መንግሥት ይህንን ጉዳይ ያስቁምልን" ሲሉ አቤቱታቸውን አቅርበዋል።

እንዲሁም ደግሞ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው። ቤተሰቦቻችን ግን ጥበቃ እያገኙ አይደለም፤ የቤተሰባችንም ሕይወት አደጋ ላይ ስለወደቀ ጥበቃ ይደረግልን ሲሉ ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ የዐቃቤ ሕግ ቀሪ ምስክሮች ለመስማት ለረቡዕ ነሐሴ 20/2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።