እስራኤል፡ ወጣቶች ከአንድ ሺህ ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ የወርቅ ሳንቲሞች አገኙ

የቅሪተ አካል ምርምር በሚካሄድበት አካባቢ በበጎ ፍቃደኝነት የሚሠሩ የእስራኤል ወጣቶች 1,100 ዓመታት ያስቆጠሩ 425 የወርቅ ሳንቲሞች አገኙ።

በማዕከላዊ እስራኤል የተገኙት የወርቅ ሳንቲሞች በሸክላ ጆግ ውስጥ ተቀብረው ነበር።

አብዛኞቹ ሳንቲሞች በጥንታዊ የእስልምና ዘመን ግዛቱ የአብሳድ ካሊፋት ክፍል ሳለ የነበሩ ሲሆኑ፤ 845 ግራም ይመዝናሉ።

በተቀበሩበት ወቅት በከፍተኛ ገንዘብ የሚገመት ዋጋ ነበራቸው። የሳንቲሞቹ ዋጋ በዘመኑ አንድ ቅንጡ ቤት ያስገዛ ነበር።

ሳንቲሙ የማን እንደነበረና ለምን ከተቀበረበት ሳይወጣ እንደቀረ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

በእስራኤል ጥንታዊ ቅርሶች ባለሥልጣን የሚሠሩት የቁፋሮው ኃላፊዎች ሊያት ናዳቭዚቭ እና ሌሊ ሃዳድ “ሳንቲሞቹን ከ1,100 ዓመታት በፊት የቀበራቸው ሰው ተመልሶ ሊወስዳቸው ሳያስብ አልቀረም። መያዣውን በቢስማር አጣብቀውት ነበር” ብለዋል።

እንደዚህ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሳንቲሞች አንድ ሥፍራ ተቀብረው ማግኘት ብዙም አልተለመደም።

“ወርቅ እጅግ ውድ ከመሆኑ የተነሳ በቁፋሮ ወቅት የተቀበረ ወርቅ ብዙ ጊዜ አናገኝም። ወርቅ እየቀለጠ ከትውልድ ወደ ትውልድ በመሸጋገር ጥቅም ላይ ይውላል” ብለዋል ተመራማሪዎቹ።

ወርቁን ካገኙ ወጣቶች አንዱ የሆነው ኦዝ ኮኸን “በጣም ድንቅ ነገር ነው የገጠመኝ። ስቆፍር ስስ ቅጠል የሚመስል ነገረ አየው። በድጋሚ ስመለከተው ግን የወርቅ ሳንቲሞች እንደሆኑ ገባኝ” ብሏል።

የወርቅ ተመራማሪው ሮበርት ኩል እንደሚሉት፤ በቁፋሮ የተገኘው የወርቅ መገበያያ ሳንቲም ብቻ ሳይሆን 270 የወርቅ ቁርጥራጮች ጭምርም ናቸው። እነዚህ ቁርጥራጮች እንደ ዝርዝር ሳንቲም የሚያገለግሉ ነበሩ።

ከወርቅ ቁርጥራጮቹ አንዱ የባዛንታይን ሥርወ መንግሥቱ ቲዎፍሎስ ምስል አለበት። ምስሉ ከኮንስታንቲሎፕ ምስል ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ በወቅቱ ሁለቱ ተቀናቃኞች መካከል አንዳች ትስስር መኖሩን የሚጠቁምም ነው።