ሴኔጋል፡ በዳካር ወደብ ያለው አሞኒየም ናይትሬት እንዲነሳላት ጠየቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቅርቡ የሊባኖሷን መዲና ቤይሩት ያናወጠው ከባድ ፍንዳታን ያስከተለው የአሞኒየም ናይትሬት ክምችት በዳካር ወደብም ስጋት ሆኗል።
ሴኔጋል ይህንን ኬሚካል የት ላድርገው? እያለች ነው።
የሴኔጋል ባለሥልጣናት 2 ሺህ 700 ቶን የሚመዝነውን ይህን ኬሚካል ከዳካር ወደብ እንዲነሳላቸው ጠይቀዋል።
በመኖሪያ አካባቢዎች አቅራቢያ ባለው ዳካር ወደብ ተከማችቶ የሚገኘው አሞኒየም ናይትሬት መጠን በቤይሩት ከነበረው ጋር የሚቀራረብ ነው ተብሏል።
ባለሥልጣናት እንደሚሉት ኬሚካሉ ወደ ጎረቤት አገሯ ማሊ ሊጓጓዝ የታቀደ 3 ሺህ ሃምሳ ቶን ኬሚካል አካል ነው።
ከዚህ ውስጥ 350 ቶን ወደ ማሊ እንደተጓዘ የወደቡ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
መንግሥት በበኩሉ የኬሚካሉ ባለቤት ኬሚካሉን ከዳካር 30 ኪሎ ሜትር በምትርቀው ዲያምኒያዶ በሚገኝ መጋዘን እንዲያስቀምጥ መጠየቃቸውን ተናግሯል።
ይሁን እንጅ የአካባቢ ሚኒስቴር በአካባቢና በማህበራዊ ሕይወት ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ጨምሮ ቦታው ለተባለው ዓላማ የሚያስፈልገውን መስፈርት አያሟላም በሚል ጥያቄውን አልተቀበለም።
የሚኒስቴሩ ባለሥልጣን ባባ ድራሜ "ኬሚካሉ ከሴኔጋል እንዲወጣ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ባለቤቱን ጠይቀናል" ሲሉ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።
የኬሚካሉ ባለቤት ማን እንደሆነ ያልተገለፀ ሲሆን በማሊም ለምን ሥራ ሊጠቀሙበት እንደሚፈልጉ የታወቀ ነገር የለም። የወደቡ ባለሥልጣናትም ኬሚካሉ ተጭኖ ወደቡ ላይ የደረሰበትን ቀን አልገለፁም።
በማሊ ፕሬዚደንት ኢብራሂም ባውባካር ኬታን ከሥልጣን ካወረደው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በኋላ ባለው ፖለቲካዊ ቀውስ ኬሚካሉን ወደዚያ ማጓጓዙን ፈታኝ ያደርገዋል። የት ይደረግ? ወዴት ይላክ? መልስ ያላገኘ ጥያቄ ሆኗል።
ቤይሩት በዚሁ ኬሚካል በተፈጠረ ፍንዳታ ሳቢያ ክፉኛ የወደመች ሲሆን ከ200 በላይ ሰዎችም ሞተዋል። በከተማዋ ዙሪያ የሚገኙ ህንፃዎችም ሳይቀሩ ወድመዋል።












