በትግራይ መራጮችን ለመመዝገብ የሞባይል መተግበሪያ ጥቅም ላይ ይውላል ተባለ

በትግራይ መራጮችን ለመመዝገብ የሞባይል መተግበሪያ ጥቅም ላይ ይውላል ተባለ።
የትግራይ ክልል ምርጫ ኮሚሽን ‘ሃራ ስርዓት ምህዳር’ ከሚሰኝ ድርጅት ጋር መራጮች የሚመዘገቡበት እና ድምጻቸውን የሚሰጡበት መተግበሪያ በጋራ እያበለጸጉ ይገኛሉ።
ይህ መተግበሪያ ለመጀመርያ ጊዜ ትናንት በመቀለ ሙከራ ተደርጎበታል። መራጮች ሞባይል ላይ በሚጫነው መተግበርያ [አፕ] የሚመዘገቡ ሲሆን፤ አንድ መራጭን ለመመዝገብ ከ30 እስከ 50 ሰከንዶች ብቻ በቂ መሆናቸውን የ‘ሃራ ስርዓት ምህዳር’ ወኪል ኃ/ስላሴ ሊላይ ተናግረዋል።
መራጮችን ለመመዝገብ የኢንተርኔት አገልግሎት እንደማያስፈልገው የተጠቀሰው መተግበሪያ፤ መራጮች ድምጽ እንዲሰጡ እንዲያስችል ተደርጎ የተሰራ መሆኑም ተጠቁሟል። የመተግበሪያው የድምጽ አሰጣጥ ስርዓት ደግሞ በሚቀጥለው እሁድ ሙከራ ይደረግበታል ሲሉ አቶ ኃ/ስላሴ ሊላይ ተናግረዋል።
ይህ መተግበሪያ በምርጫ ዕለት አንድ መራጭ ብቻውን ወደ ምስጢራዊ የድምጽ መስጫ ቦታ ገብቶ ከወረቀት ንክኪ ነጻ በሆነ መልኩ በታብሌት በመታገዝ ‘በዲጂታል ኮሮጆ’ ድምጹን እንዲሰጥ ያስችላል ሲሉ አቶ ኃ/ስላሴ ተናግረዋል።
በትግራይ የሚካሄደው ክልላዊ ምርጫ ጳጉሜ 4 እንዲሆን መወሰኑን የክልሉ ምርጫ ኮሚሽን ማስታወቁ ይታወሳል። የክልሉ ምርጫ ኮሚሽን ይፋ ባደረገው የግዜ ሰሌዳ መሠረት የመራጮች ምዝገባ ከነሐሴ 15-22 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን፤ባለፈው ሳምንት የተጀመረው የምርጫ ቅስቀሳ ደግሞ ነሐሴ 29 ይጠናቀቃል ተብሏል።








