ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤልና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ስልክ መደዋወል ጀመሩ
ሁለቱ አገሮች ወደዚህ ስምምነት ለመምጣት ዓመታት ወስዶባቸዋል፡፡ አገራቱ በመሀላቸው ያለውን ግንኙነት ጤናማ ለማድረግ የተስማሙት ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡
ይህን ተከትሎም ከረዥም ጊዜ በኋላ እስራኤልና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ያለ ሦስተኛ ወገን በቀጥታ በቀጭኑ ሽቦ መደዋወል ጀምረዋል፡፡ የቀጥታ ስልክ አገልግሎቱ መጀመሩን ይፋ ለማድረግ በቅድሚያ የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ‹‹ሀሎ እንደምን አለህ›› የሚል መልእክት መለዋወጣቸው ተዘግቧል፡፡
አሜሪካ አሸማገለችው በተባለው በዚህ ታሪካዊ ስምምነት ሁለቱ አገሮች ለመቀራረብ የወሰኑት ባለፈው ሐሙስ ነበር፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ እስራኤል ከአንድ የአረብ አገር ጋር የሰላም ስምምነት ስትፈራረም የሐሙሱ በታሪክ ሦስተኛው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ከእስራኤል ጋር መሰል የሰላም ስምምነት የፈረሙት አረብ አገራት ግብጽ እና ጆርዳን ብቻ ናቸው።
በርካታ የዓለም አገራት ስምምነቱን በበጎ የተመለከቱት ሲሆን ፍልስጤም፣ ኢራንና ቱርክ ግን የተባበሩት አረብ ኢምሬትስን እርምጃ ‹‹ክህደት›› ብለውታል፡፡ በዚህ ስምምነት መሰረት እስራኤል በግድ እጠቀልለዋለሁ ያለችውን የዌስት ባንክ የተወነ አካባቢ ወደራሷ ግዛት ማድረጉን እርግፍ አድርጋ ትተዋለች፡፡
የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋቢ አሽከናዚ ትናንት በትዊተር ሴሌዳቸው ‹‹…በስልክ አውርተናል፤ በአካል በቅርቡ እንገናኛለን›› ብለዋል፡፡ በአካል እንገናኛለን ያሉት የኢምሬትሱን አቻቸውን አብዱላሂ ቢን ዛይድ አል ናህያንን ነው፡፡
የእስራኤል የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ዮዋዝ ህንደል ለረዥም ጊዜ ዝግ ሆኖ የቆየው በ+972 የሚጀምር ቁጥር እቀባው ተነስቶለታል ብለዋል፡፡ ‹‹በዚህም የተባበሩት መንግሥታትን እንኳን ደስ አለን እላለሁ፤ ብዙ የኢኮኖሚ አማራጮች ከዚህ በኋላ ክፍት ናቸው›› ሲሉም ያላቸውን ተስፋ ገልጠዋል ሚኒስትሩ፡፡
ሁለቱ ወገኖች ሙሉ ስምምነቱን በዋሺንግተን ተገኝተው በሚቀጥሉት ሦስት ሳምንታት ውስጥ ይፈርማሉ ተብሎ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ግንኙነታቸውን ጤናማ የማድረጉ ስምምነት ውስጥ ሁለቱም አገራት ኤምባሲዎቻቸውን በሌላ አገር የመክፈት ስምምነትን ይጨምራል፡፡
አገራቱ ገና ይፋዊ ስምምነቱን ከመፈረማቸው የኮቪድ-19 ምርመራ ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተሰምቷል፡፡ እስከዛሬ እስራኤል ከገልፍ አረብ አገራት ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት አልነበራትም፡፡ ሆኖም ግን የጋራ ጠላት ተደርጋ የምትታሰበው ኢራን አገራቱ ሳይፈልጉም ቢሆን ተቀራርበው እንዲሰሩ አድርጓቸው ቆይቷል፡፡
የትራምፕ ልዩ አማካሪ ጄሪድ ኩሽነር ለሲቢኤስ እንደተናገረው ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ አገራቱን ለማቀራረብ ደፋ ቀና ሲሉ ነበር ብሏል፡፡ ይህ ስምምነት የፍልስጤሙን መሪ ሙሐመድ አባስን ያስደነገጠ ነበር ተብሏል፡፡
‹ወዳጆቻችን ከጀርባ በጩቤ ወጉን ብለዋል› ብለዋል አንድ የሙሐመድ አባስ አማካሪ ለአልጀዚራ፡፡ ፕሬዝዳንት አባስም ስምምነቱን ‹‹ክህደት›› ሲሉ ጠርተውታል፡፡
እስራኤል አገር ሆና ከተፈጠረች ከ1948 ወዲህ ኢምሬቶችን ጨምሮ ከሦስት የአረብ አገራት ጋር ብቻ ሰላም ስምምነትን ፈርማለች፡፡ ይህም በ1979 ከግብጽ እና በ1994 ከጆርዳን ጋር ነው፡፡
የአረብ ሊግ አባል የሆነችው ሞሪታኒያ ከእስራኤል ጋር ተቀራርባ ስትሰራ ቆይታለች፡፡ ሆኖም አሁን ግንኙነቱ ሻክሯል፡፡ ዶናልድ ትራምፕ ሌሎች አረብ ሙስሊም አገራትም ከእስራኤል ጋር አብረው እንዲሰሩ እናደርጋለን ብለዋል፡፡
ቤንያሚን ናታንያሁ በበኩላቸው ይሄ ዌስት ባንክ አካባቢ ያሉ ተጨማሪ መሬቶችን የመጠቅለሉን ነገር አዘገየሁት እንጂ አልተውኩትም ብለዋል ለአገራቸው ሚዲያ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም በኢምሬቶችና በእስራኤል መካከል ስለተደረሰው ስምምነት ያላቸው ድጋፍ በትዊተር ሰሌዳቸው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ሁለቱንም አገራት እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋቸዋል፡፡