ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ ምርጫው ይጭበረበራል ብለው የፈሩት ለምንድነው?
ትራምፕ የኅዳሩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ኮሮጆው ይገለበጣል የሚሉት ለምንድነው? በመጪው ኅዳር አሜሪካዊያን ዶናልድ ትራምፕን ያሰናብቷቸዋል ወይም ያጸኗቸዋል፡፡
ይህን ለማድረግ ድምጽ መስጠት አለባቸው። ድምጽ የሚሰጡት ደግሞ አንድም በድምጽ መስጫ ጣቢያ በመገኘት ሲሆን ሌላው ደግሞ ድምጻቸውን በፖስታ ቤት በመላክ ነው። ሁለተኛው ዘዴ ‹‹ሜይል ኢን ባሎት›› እያሉ ይጠሩታል፣ የአገሬው ሰዎች።
አሁን አሜሪካ በወረርሽኝ ውስጥ ናት። 5 ሚሊዮን ተኩል ሕዝቧ ታሞባታል። 170ሺህ ሞቶባታል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ መራጩን ሕዝብ ወደ ምርጫ ጣቢያ እየሄድክ ተሰልፈህ ድምጽ ስጥ ማለት ብዙም ስሜት የሚሰጥ ጉዳይ አልሆነም። ይህም በሁለት ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡
አንዱ በምርጫ ጣቢያዎች የሚፈጠረውን መተፋፈግ፣ የድምጽ መስጫ ቁስ ንክኪና ማኅበራዊ ርቀትን አለመጠበቅ በርካታ ሰዎችን ለጤና ችግር ሊዳርግ ይችላል። ሁለተኛ ምርጫው እንደተለመደው በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ድምጽ የሚሰጥበት ከሆነ በርካታ ዜጎች መምረጥ እየፈለጉ ነገር ግን ወደ ምርጫ ጣቢያ መሄድ የጤና ቀውስ ያስከትልብናል ብለው በመስጋት ብቻ ይህንኑ ላያደርጉ ይችላሉ።
ይህ ደግሞ የምርጫውን ውጤት እንዳልተጠበቀው ሊያደርገው ይችላል። ፖለቲካ አዋቂዎች የሚሉት ታዲያ ትራምፕ የፖስታ ድምጽ አሰጣጥ እንዳይኖር የፈለጉት የርሳቸው ደጋፊዎች ስለ ወረርሽኙ ደንታም ስለሌላቸው ድምጽ መስጫ ጣቢያ ለመውጣት አይሰጉም።
በፖስታ ድምጽ መስጠት አዲስ ነገር ነው?
ይህ የፖስታ ድምጽ አሰጣጥ በአሜሪካ ምርጫ ሥርዓት ውስጥ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ሲሰራበት የኖረ ነው፡፡
ብዙ ግዛቶች ይህን ይፈቅዳሉ፡፡ አብሰንቲ ባሎት ይሉታል፡፡ ‹‹አብሰንቲ ባሎት›› የሚባለው አንድ ሰው በጤና፣ በሥራ ወይም በሌላ በማንኛውም ምክንያት ምርጫ ጣቢያ ሄዶ ድምጽ መስጠት እንደማይችል ሲገነዘብ፣ ‹‹ምርጫ ጣቢያ ሄጄ ድምጽ መስጠት ስለማልችል በአድራሻዬ ቅጽ መጥቶልኝ ቅጹን ሞልቼ በፖስታ ቤት በኩል ድምጼን ልላክ›› ብሎ የሚጠይቅበት አሰራር ነው፡፡
ይህ አሰራር በማረሚያ ቤት ሆነው ድምጽ የመስጠት መብት ያላቸው፣ በሰላም አስከባሪ ጦር ውስጥ በተልእኮ ሌላ ቦታ የሚገኙ የሰራዊት አባላት፣ በትምህርት ምክንያት ከመኖርያ አድራሻቸው የራቁ አሜሪካዊያን ወይም በሌላ ምክንያት በምርጫው ዕለት ምርጫ ለመስጠት በተመዘገቡበት አድራሻ መገኘት ያልቻሉ አሜሪካዊያን ‹‹አብሰንቲ ባሎት›› የምርጫ ደምጽ መስጫ አማራጭን በመጠቀም ሊመርጡ ይችላሉ፡፡
በአጭሩ አብሰንቲ-ባሎት የሚባለው መራጩ በአንዳች ምክንያት የምርጫ ጣቢያ ሄዶ ድምጽ መስጠት እንደማይችል በመገንዘብ በፖስታ ቤት ድምጽን ሲሰጥ ነው፡፡‹‹ሜይል-ኢን-ባሎት›› የሚባለው አብሰንቲ ባሎትንም ሆነ እንዲሁ ግዛቱ ያን አሰራር ስለሚጠቀም ሊሆን ይችላል በማንኛውም ምክንያት ብቻ ድምጽ ምርጫ ጣቢያ በመገኘት ሳይሆን በፖስታ ቤት በኩል የሚሰጥበት አሰራር ጥቅል የወል ስም ነው፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ለምን የፖስታ ቤት ምርጫን ጠሉት?
ትራምፕ በፖስታ ቤት ድምጽ ከተሰጠ ምርጫው ይጭበረበርብኛል ነው የሚሉት፡፡
የአሜሪካ ፖለቲካ አዋቂዎች እንደሚሉት ግን ዶናልድ ትራምፕ ሰዎች ወደ ድምጽ መስጫ ጣቢያ እየሄዱ እንዲመርጡ የሚፈልጉበት ምክንያት በርካታ አሜሪካዊያን በፖስታ ቤት በኩል ድምጻቸውን ከላኩ የዲሞክራት እጩዎች በርከት ያለ ድምጽ ያገኛሉ ብለው ስለሰጉ ነው፡፡
በዚህ የተነሳም የፖስታ ምርጫን ማጥላላት ይዘዋል፡፡ ‹‹የፖስታ ምርጫ በአሜሪካ ታሪክ ከፍተኛ የምርጫ መጭበርበር ያስከትላል፡፡ እኔ ተናግሪያለሁ ኋላ›› እያሉ ነው ትራምፕ፡፡ ሆኖም ጥናቶች የሚያሳዩት ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡
በፖስታ ቤት በኩል የሚደረጉ ድምጽ አሰጣጦች ለመጭበርበር ያላቸው ዕድል በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ በ2016 በነበረው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ (ዶናልድ ትራምፕን ነጩ ቤተ መንግሥት ባስገባው ምርጫ ማለት ነው) ከመራጩ አንድ አራተኛ የሚሆነው ድምጹን የሰጠው በዚሁ መንገድ ነው፡፡
የትኞቹ ግዛቶች የትኞቹን አሰራሮች ይመርጣሉ?
ግዛቶች ሁሉም የራሳቸው የምርጫ አሰራር ድምብና ሥርዓት አላቸው፡፡
ይህን ተከትለው ባለው ነባራዊ ሁኔታ ዜጎች በፖስታ ቤት በኩል ድምጻቸውን እንዲሰጡ የሚያመቻቹ ግዛቶች እንደሚበረክቱ ይጠበቃል፡፡ አሁን ባለው አሰራር ምርጫ ሙሉ በሙሉ በፖስታ ድምጽ የሚሰጥባቸው አምስት ትልልቅ ግዛቶች አሉ፡፡ ካሊፎርኒያን ጨምሮ፡፡
በፖስታ ድምጽ ለመስጠት ምንም ምክንያት የማይጠየቅበትና የዜጎች ፍላጎት ብቻ እንደሆነ ያወጁ ደግሞ 28 የአሜሪካ ግዛቶች አሉ፡፡ ሌሎች 15 ግዛቶች ግን ዜጎች በፖስታ ድምጽ እንስጥ ካሉ ምክንያት እንዲሰጡ ይጠይቃሉ፡፡
አሁን ባለው አሰራር 6 ግዛቶች የኅዳሩን ምርጫ ሙሉ በሙሉ በፖስታ ቤት በኩል እንዲሆን የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ዩታ፣ ሃዋይ፣ ኮሎራዶ፣ ኦሪገንና ዋሺንግተን እንዲሁም ሰፊው ካሊፎርኒያ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ይገኛሉ፡፡
በነዚህ ስድስት ግዛቶች በአካል ድምጽ መስጫ ጣቢያ የለም ባይባልም በጣም ውስን ነው፡፡ እነዚህ ግዛቶች አስቀድመው ለመራጮች ቅጽ በአድራሻ በመላክ የምርጫው ቀን መራጩ ድምጹን በፖስታ ቤት በኩል እንዲልክ ያመቻቹ ናቸው፡፡
ከአሜሪካ ግዛቶች ግማሾቹ ማንኛውም ዜጋ ድምጼን በፖስታ ነው መላክ የምፈልገው ካለ ይህንኑ ወዲያውኑ፣ ማስረጃ ሳይጠይቁ ይፈቅዳሉ፡፡ የተቀሩት ግዛቶች ግን አንድ ሰው በፖስታ ቤት በኩል ድምጼን ልስጥ ካለ አሳማኝ ምክንያት እንዲያቀርብ የሚፈልጉ ናቸው፡፡
ለምሳሌ ዕድሜው ከ65 በላይ መሆን፣ ወይም የጤና እክል ወይም ምርጫ ለመስጠት በተመዘገቡበት አድራሸ በሥራ ምክንያት አለመኖር ወይም ሌላ፡፡
የሚገርመው ምርጫው በፖስታ ቤት ከሆነ ይጭበረበራል የሚሉት ዶናልድ ትራምፕ ራሳቸው የፍሎሪዳን የፕራይመሪ ምርጫ ድምጽ የሰጡት በፖስታ ቤት በኩል መሆኑ ነው፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሥልጣኑ የላቸውም እንጂ ምርጫ ይራዘም የሚል ሐሳብም አቅርበው ነበር፡፡ አዲስ የተሾሙት የአሜሪካ የፖስታ ቤት አለቃ ሉዊስ ዲ ጆይ (ጥብቅ የትራምፕ ደጋፊ እንደሆኑ ይነገራል) ምርጫ በፖስታ ቤት በኩል ከሆነ ሚሊዮን ድምጾች በወቅቱ ላይደርሱ ይችላሉ ሲሉ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡
ይህም ዶናልድ ትራምፕን ለመደገፍ ያደረጉት እንደሆነ በመታሰቡ የታችኛውም ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፒሎሲ ፖስታ ቤቱን እናድን የሚል ጥሪ ለምክር ቤት አባላት አስተላልፈዋል፡፡