ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ልዩ ኃይል፡ የአገር አንድነት ስጋት ወይስ የሕዝብ ደኅንነት ዋስትና?
በኢትዮጵያ የሚገኙ ክልሎች የራሳቸውን የልዩ ኃይል ፖሊስ ማደራጀት ከጀመሩ ዓመታት ቢሆናቸውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ መደበኛ ሠራዊት በሚመስል መልኩ እየሰለጠኑና እየተደራጁ መሆናቸው ይነገራል።
ከዚህ አንጻር በርካቶች፤ ክልሎች የራሳቸውን ልዩ ኃይል አደራጅተውና አስታጥቀው ማሰማራታቸው ለአገር ደኅንነት አደጋ ነው፤ የእነዚህ ኃይሎች አደረጃጀትም ሕጋዊ መሠረት የሌለው ነው በማለት ይከራከራሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ የልዩ ኃይል ፖሊሶችን ጥቅም ከግምት በማስገባት የአንድን ክልል ሕዝብ ደኅንነት ለማስጠበቅ ከፖሊስ ባሻገር ይህ ሠራዊት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበርክት እንደሚችል የሚሞግቱ አሉ።
በኢትዮጵያ የልዩ ፖሊስ አመሰራረት ምን ይመስላል?
የአምነስቲ የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ አጥኚ የሆኑት አቶ ፍሰሐ ተክሌ፤ በኢትዮጵያ የተመሰረተው ልዩ ኃይል በ1998 ዓ.ም የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ መሆኑን ይናገራሉ።
"ከኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ጋር ከነበረውን የሽምቅ ውጊያ ጋር በተያያዘ ነበር ይህ ልዩ ኃይል የተደራጀው። ከዚያም በኋላ በኦሮሚያና በአማራ እንዲሁም በሌሎች ክልሎችም ልምዱ ተስፋፍቶ ቀጥሏል” ይላሉ።
የሶማሌ ክልል ተወላጅና ሁለት ጊዜ የሕዝብ ተወካዮች የምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ጀማል ድሪ ሃሊስ ከዚህ ቀደም የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ አመሰራረትን በተመለከተ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በክልሉ የነበረውን የአማጺያን እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር ነበር።
''በአካባቢው ይንቀሳቀስ የነበረውን የኦብነግ ኃይልን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለመደምሰስ ብዙ ጥረት አድርጎ ውጤታማ መሆን አልቻለም'' የሚሉት አቶ ጀማል፤ በወቅቱ በክልሉ የተሰማራው የአገር መከላከያ ሠራዊት የአካባቢውን ቋንቋና ባህል ስለማያውቅ የአማጺያኑን ከሲቪሉ ሕዝብ ለመለየት አልቻለም ነበር ይላሉ።
በ2007 (እአአ) ላይ የክልሉን ፖለቲካዊ ምህዳር የቀየር ሁኔታ እንደተከሰተ የሚናገሩት አቲ ጀማል "ኦብነግ ነዳጅ ፍለጋ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ከ70 በላይ ቻይናውያንና በርካታ ኢትዮጵያውያንን ገደለ። በዚህም የፌደራሉ መንግሥት ኦብነግ ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ተነሳ” ይላሉ።
ለዚህም ሁነኛ አማራጭ የነበረው በሶማሌ ክልል ችግር ሆነው የቆዩትን ሥራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀት ሰልጠና ሰጥቶና አስታጥቆ ኦብነግ ላይ ማዝመትና የአማጺውን እንቅስቃሴ በእነዚህ ወጣቶች መቆጣጠር እንደነበረ አቶ ጀማል አስታውሰዋል።
የልዩ ኃይል አመሰራረት ሕጋዊ መሠረት
ከልዩ ፖሊስ አመሰራረት ጋር አብሮ ከሚነሱት ጉዳዮች መካከል እንዱ ሕጋዊ መሠረቱ ነው። የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 52 የክልሎች ስልጣንና ተግባር ይደነግጋል።
የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 52/ሰ ክልሎች የክልላቸውን የፖሊስ ኃይል ያደራጃሉ፣ ይመራሉ፣ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ያስጠብቃሉ ይላል። ይሁን እንጂ ይህ የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ ለአተረጓጎም ክፍት መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፌደራሊዝምና የሰብዓዊ መብቶች መምህር ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር)ይናገራሉ።
"ከመደበኛ ፖሊሱ በተጨማሪ ክልሎች ሌላ ፖሊስ እንዲያደረጁና እንዲያሰማሩ ይፈቅዳል ብለው የሚተረጉሙ አሉ። የለም ይህ አንቀጽ የሚለው ክልሎች ሰላምና ጸጥታ የሚያስከብሩት መደበኛ ፖሊስን ተጠቅመው ነው ብለው የሚከራከሩ ወገኖችም አሉ" ይላሉ።
ስለዚህም ኃይል አመሰራረት ሙሉ በሙሉ ሕገ-ወጥ ነው ለማለትም ሆነ ሕጋዊ ነው ለማለት አስቸጋሪ እንደሆነ ሲሳይ (ዶ/ር) ያስረዳሉ። "ሙሉ በሙሉ የሕግ መሠረት የለውም ብሎ ለመከራከር ያስቸግራል። ሕገ-መንግሥታዊ መሠረት አለው ለማለትም ድንጋጌዎች ግልጽነት ይጎድላቸዋል።"
የፌደራሉ መንግሥት ከትጥቅ አያያዝና አደረጃጀት ጋር የተያያዘ ግልጽ ፖሊሲ በማውጣት ሕገ-መንግሥቱ ላይ የተጠቀሰውን አንቀጽ በዝርዝር ሕግ መብራራት እንደሚገባውም ሲሳይ (ዶ/ር) ይናገራሉ።
የመከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ጀነራል አደም መሐመድ ግን ከቀናት በፊት በብሔራዊው ቴሌቪዥን ላይ፤ የልዩ ኃይሎች አመሰራረት ሕጋዊ ማዕቀፍ እንደሌለው ተናግረዋል። "የልዩ ኃይሉ አደረጃጀት ከሕገ-መንግሥቱ አንጻር ከታየ ሕጋዊ ማዕቀፍ የለውም" ብለዋል ኢታማዦር ሹሙ።
ልዩ ኃይሎች ወገንተኛ ናቸው
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሸናል በኢትዮጵያ በተለይ በሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል መመስረት ከጀመረ ወዲህ፤ በልዩ ፖሊሶች የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሲመዘግብ ቆይቷል።
የክልል ልዩ ኃይሎች የሚወስዷቸው እርምጃዎች ላይ ወገንተኝነት ይታይባቸዋል። በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰትም ይፈጽማሉ፤ ስለዚህም የክልል ልዩ ኃይሎች መበተን አለባቸው በማለት የሚሞግቱ በርካቶች ናቸው።
ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ-ኢዜማ ይገኝበታል። የፓርቲው የሕዝብ ግነኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ፤ "ፓርቲያችን ከልዩ ኃይል ፖሊስ አንጻር ያለው ችግር የመጀመሪያው መሠረታዊ ጉዳይ ከአመሰራረቱ ጋር ይያያዛል” ይላሉ። አቶ ናትናኤል የልዩ ፖሊስ አመሰራረት ምንም አይነት ሕጋዊ መሠረት እንደሌለው ይናገራሉ።
"ከዚህ በተጨማሪ ኃይሉ ተደራጅቶ ሲንቀሳቀስ መታዘብ እንደቻልነው፤ እራሱን [ልዩ ኃይል] የአንድ ብሔራ ጠባቂ አድርጎ በማየት በተደራጀበት ክልል የሚኖሩ የሌላ ዘውግ ማንነት ያላቸውን ማጥቂያ መሳሪያ ሲሆን፣ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር እንቅፋት ሲሆን ተመልክተናል" ይላሉ።
የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ አጥኚው አቶ ፍሰሐም፤ ከዚህ ቀደም የክልል ልዩ ኃይሎች በወሰዷቸው እርምጃዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን ያስታውሳሉ። አቶ ፍሰሐ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በሶማሌ ክልል እንዲሁም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ ድንበር ላይ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸሙን ይናገራሉ።
የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይልም አምነስቲ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ላይ በሁሉቱ የጉጂ ዞኖች ላይ፤ "ከሕግ ውጪ ሰዎችን እንደሚገድሉና ቤቶች እንደሚያቃጥሉ መዝግበናል" ብለዋል የአምነስቲው አጥኚ።
የአማራ ክልል ልዩ ፖሊስም በተመሳሳይ፤ በተለያዩ ቦታዎች በተከሰቱ ግጭቶች ላይ ተሳትፎ እንደነበረው አቶ ፍሰሐ ጠቅሰው "ለአንድ ወገን በመወገን ጥቃቶችን አድርሰዋል፣ ቤቶችን አቀጥለዋል፣ ሰዎችንም ከሕግ ውጪ አስረዋል" ይላሉ።
ልዩ ኃይል መበተን አለበት
የክልሎች ልዩ ኃይል የሚያደርሰውን ጥፋት ለማስቆም፤ የፌደራሉ መንግሥት በየክልሉ ያሉትን የተደራጀና የታጠቀን ልዩ ኃይል መበተን እንደሚኖርበት የኢዜማው አቶ ናትናኤል እና የአምነስቲው አጥኚ አቶ ፍሰሐ ይሞግታሉ።
"የክልል ልዩ ኃይል የሚባለው ፈርሶ ወይ ወደ መደበኛ ፖሊስ፣ ወይ ወደ መከላከያ ሠራዊት ወይም ደግሞ ወደ ፌደራል ፖሊስ ውስጥ እንዲጠቃለልና በዚያ ዕዝ ስር እንዲተዳደር ነው በተደጋጋሚ ስንጠይቅ የቆየነው" ይላሉ የኢዜማ የሕዝብ ግነኙነት ኃላፊው አቶ ናትናኤል።
አቶ ፍሰሐም በበኩላቸው፤ “መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥቃት ከማድረሳቸውና ለተፈጸሙት ድርጊቶች ተጠያቂ ሲሆን ከአለማየታችን አንጻር ይህ የፖሊስ ኃይል እንዲበተንና አስፈላጊ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀናል" ሲሉ በአምነስቲ በኩል የቀረበውን ሃሳብ ጠቅሰዋለ።
የልዩ ፖሊስ ኃይል ወሳኝነት አያጠያይቅም
የክልል ልዩ ኃይሎች ይበተኑ፤ የሚለው ሃሳብ ለጸጥታ አማካሪው ለብርጋዴየር ጀነራል ኃይሉ ጎንፋ የሚዋጥ አይደለም። ብ/ጀ ኃይሉ የልዩ ፖሊሶች ወሳኝነት ላይ ጥርጣሬ የላቸውም። በልዩ ኃይል ተፈጸሙ ለሚባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም ምክንያት አስተዳደራዊ ችግር እንጂ የልዩ ኃይሉ አይደለም ይላሉ።
በክልሎች ያሉት የልዩ ኃይል ሠራዊት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ይፈጽማሉ እንዲሁም ወገንተኛ ናቸው ለሚለው ችግሩ፤ “የመንግሥታዊ መዋቅር፣ የቢሮክራሲ እና የአስተዳደር ችግር ነው እንጂ የልዩ ኃይሉ ችግር አይደለም” ይላሉ።
ብ/ጀ ኃይሉ ሃሳባቸውን በዝርዝር ሲያስረዱ “ልዩ ኃይል በትዕዛዝ የሚሄድ ኃይል ነው። ልዩ ኃይሉን የሚመሩ ክልሎች ወይም ፓርቲዎች በትክክል በክልሎችና በፌደራል ሕገ-መንግሥት መሠረት ሕግን ተከትለው ልዩ ኃይሉን ቢመሩ ችግር አይፈጠርም” ብለው ያምናሉ።
ለዚህም እንደመፍትሔ የሚያስቀምጡት ለሚከሰቱ ችግሮች "የሕግ የበላይነት በሠራዊቱ አዛዦች ላይ ቢተገበር፤ ልዩ ኃይሉም ከዚያ አንጻር ነው የሚቃኘው" ይላሉ።
ብ/ጀ ኃይሉ "በአንዳንድ ክልሎች የተስተዋሉት ችግሮች እንዳይከሰቱ የልዩ ኃይሉን ተልዕኮ ማስተካከልም ያስፈልጋል" ባይ ናቸው። "የክልል ልዩ ኃይል ብቻ ሳይሆን የሚሰጠው ተልዕኮው ከተበላሸ መከላከያም ሊበላሽ ይችላል።"
በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በፌደራል ሥርዓት በሚተዳደሩ አገራት ውስጥም ይህ አይነት አደረጃጀት እንዳለ የሚያስረዱት ብ/ጀ ኃይሉ፤ በኢትዮጵያ ያውን የልዩ ኃይል ፖሊስ ኃይል ተልዕኮና ኃላፊነት ማጥራት፣ እንዲሁም አባላቱ የሚሰለጥኑበት የጦር ሥነ ምግባርና የጦር ርዕዮተ-ዓለም ዳግም መከለስ እንዳለበት ያሳስባሉ።
መከላከያና ፌደራል ፖሊስ እያሉ ልዩ ፖሊስ ለምን ተፈጠረ?
በአንድ ክልል የሚከሰትን የጸጥታ መደፍረስን ፖሊስ ወይም የሚሊሻ የጸጥታ መዋቅር ማስቆም ቢሳነው የፌደራል ፖሊስ አልያም መከላከያ ሠራዊት ወደ ክልሉ ዘልቆ በመግባት ሰላም የሚያስከብሩበት ዕድል እያለ ልዩ ኃይልን መመሠረት አስፈላጊነት በተመለከተ በበርካቶች ዘንድ ጥያቄ ይነሳል።
ብርጋዴየር ጀነራል ኃይሉ ጎንፋ እንደሚሉት የፖሊስ መደበኛ ሥራ የተለመደው የወንጀል መካላከል ሥራ እንደሆነ ጠቅሰው፤ የመከላከያ ሠራዊት ሥራም ድንበር ላይ ሆኖ የውጪ ጠላትን መከላከል ነው ይላሉ።
ከዚህ አንጻር የልዩ ፖሊስ ተልዕኮም የተደራጁ ኃይሎችን መመከት እንደሆነ በመጥቀስ "ፖሊስ የዕለት ተዕለት ጥቃቅን የሆኑ ቴክኒካል ሥራዎችን ነው የሚሰራው። እንደ ኢትዮጵያ ሰፊ የቆዳ ስፋትባለ ባለው አገር ውስጥ ያለን ግዙፍ መከላከያ ሠራዊትን አንድን የተደራጀ ኃይል ለመደምሰስ ከድንበር ማንቀሳቀስ አዋጭ አይደለም" በማለት በክልል ያሉ ልዩ ኃይሎችን አስፈላጊነት ይጠቅሳሉ።
ብርጋዴር ጀነራል ኃይሉ ጎንፋ ጨማረውም አንድ ኅብረተሰብ ውስጥ የሚንቀሳቀስን የተደራጀ ኃይል ለመቆጣጠርና ለመደምሰስ፤ የመከላከያ ሠራዊትን ከመጠቀም ይልቅ፤ የማኅበረሰቡን ባህል፣ ባህሪና ሥነ-ልቦና የሚረዳ ኃይል ማደራጀቱ ለሚተገበሩ ተልዕኮዎች ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ያስረዳሉ።
ልዩ ኃይሎች የትጥቅ ሁኔታ
በቅርቡ የትግራይ ክልል ልዩ ፖሊስ ባካሄዳቸው ወታደራዊ ትዕይነት ላይ፤ የልዩ ኃይል አባላቱ መካከለኛ እና የቡድን የጦር መሳሪያዎችን ታጥቀው ታይተዋል።
የሌሎች ክልል ልዩ ፖሊሶችም በተመሳሳይ የቡድን የጦር መሳሪያዎችን ታጥቀው እንደሚገኙ በመጥቀስ፤ ልዩ ፖሊሶች ከሚሰጣቸው ተልዕኮ አንጻር የታጠቁት የጦር መሳሪያ ከባድ መሆኑን ብርጋዴር ጀነራል ኃይሉ ጎንፋ ይናገራሉ።
የመከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል አደም መሐመድ ግን ለብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲናገሩ ልዩ ፖሊሶች በኃይል ታጥቀዋል ማለት አይቻልም ብለዋል።
“ልዩ ኃይሎች ከባድ የጦር መሳሪያ ታጥቀዋል ሲባል ግራ ይገባኛል። የትጥቅ ደረጃ አለ ማለት ባይቻልም፤ ከባድ ጦር መሳሪያ የተባለው የቡድን መሳሪያ ለማለት ተፈልጎ ይመስለኛል። የቡድን መሳሪያ የላቸው የክልል ልዩ ኃይሎች ሊኖሩ ይችላሉ" በማለት የትጥቁን ዓይነት ገልጸውታል፤ ኢታማዦር ሹሙ።