ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ኮቪድ-19 ያነሳሳቸው አስሩ የአፍሪካውያን ፈጠራዎች
የኮሮናቫይረስ በቻይናዋ ዉሃን ከተከሰተ ዕለት ጀምሮ የአፍሪካ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል የሚሉ በርካታ መላምቶች ስለ አህጉሪቷ እናውቃለን ከሚሉ አካላት ተሰምቷል።
በአፍሪካ ቫይረሱ በመጀመሪኣ ግብጽ ውስጥ ከተመዘገበበት የካቲት 6/2012 ዓ.ም በፊትም ለምን ወደ አህጉሪቱ ለመግባት ዘገየ? ብለው ከሚጠይቁ አንስቶ ወረርሽኙ ከተዛመተ የአፍሪካውያን መጥፊያ እንደሆነም ተተንብዮ ነበር።
ሆኖም አፍሪካውያን ሊያልቁ ነው ከሚሉ ትንበያዎች ባሻገር አሁን አህጉሪቱ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ከሚሊዮን ተሻግሯል። አፍሪካውያንም እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም በርካቶችም ወረርሽኙን ለመታገል የራሳቸውን ፈጠራዎች እያበረከቱ ነው። ከእነዚህም መካከል አስሩን እነሆ፡
- የሮቦት ዶክተር
በሴኔጋል የሚገኙ የዳካር ፖሊቴክኒክ ተማሪዎች ሁለገብ ሮቦት ሰርተዋል። በኮሮናቫይረስ የተያዙ ህሙማን ወደ ተንከባቢዎቻቸው ቫይረሱን እንዳያስተላልፉ ስጋትን የሚቀንስ ነው።
ሮቦቱ ካሜራ ተገጥሞለታል፤ መተግበሪያም የተጫነለት ሲሆን በሩቅም ሆኖ መቆጣጠር ይቻላል። ሮቦቱ ከክፍል ወደ ክፍል እየተዘዋወረም በለይቶ ማቆያ ያሉ ህሙማን ሙቀት ይለካል፣ መድኃኒት፣ ምግብ፣ ውሃና ሌላም አስፈላጊም ነገሮችን ያቀርባል።
- አውቶማቲክ እጅ መታጠቢያ
በዘጠኝ ዓመቱ ታዳጊ ስቴፈን ዋሙኮታ ከእንጨት የተሰራ የእጅ መታጠቢያ ፈጥሯል። ኬንያዊው ተማሪ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሚልም ንክኪን ለማስወገድም አልሞ ነው የሰራው።
ተጠቃሚዎች በእግራቸው መታጠቢያው ላይ የተገጠመለትን መርገጫ በመጫንም እጃቸውን መታጠብ የሚችሉበት ዘዴ ነው። ሰዎች ምንም ሳይነኩም እጃቸውን በቀላሉ መታጠብ ይችላሉ። ለዚህ ፈጠራውም ታዳጊው ፕሬዚዳንታዊ ሽልማት ተሰጥቶታል።
- ተንቀሳቃሹ ቬንትሌተር
የኮሮናቫይረስ የማኅበረሰብ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ባለባት ናይጄሪያ ለፅኑ ህሙማን የሚሆን መታከሚያ ክፍልም ሆነ ቬንትሌተር እጥረት እንዳለ የተገነዘበው ናይጄሪያዊው ወጣት ችግሩን ለመቅረፍ የራሱን ፈጠራ አበርክቷል።
የ20 ዓመቱ የምህንድስና ተማሪ ኡስማን ዳልሃቱ ተንቀሳቃሽ አውቶማቲክ ቬንትሌተር ሰርቷል። በኮሮናቫይረስ በጠና የታመሙ ሰዎች የመተንፈስ እክል ስለሚገጥማቸውም በቬንትሌተሩ እገዛ እንዲተነፍሱም ይደረጋሉ። በአሁኑም ወቅት 20 ቬንትሌተሮችን ለመስራት እቅድ አለው።
- 3ዲ የጭምብል ማተሚያ
ናታሊ ራፊል በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው ሰው ሰራሽ ልህቀት (አርቲፊሻል ኢንለጀንስ) ላይ የሚሰራ ሮቦትስ ካን ቲንክ (ሮቦቶች ማሰብ ይችላሉ) የተሰኘ ድርጅት መስራች ናት።
በአሁኑም ሰዓት 3ዲን [ባለሦስት አውታር] በመጠቀም በቀን 100 ጭምብሎችን ታትማለች [ታመርታለች]፤ እነዚህንም ጭምብሎች በጆሃንስበርግ ለሚገኙ ትልልቅ ሆስፒታሎችም ታከፋፍላለች።
በአፍሪካ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ቀዳሚ በሆነችው ደቡብ አፍሪካ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።
- በፀሐይ ብርሃን የሚሰራው የእጅ መታጠቢያ
ጋና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ስርጭት ለመቆጣጠር እንቅስቃሴዎችን አግዳለች። መንግሥት ካሳለፋቸው መመሪያዎች በተጨማሪ የድርሻችንን ማበርከት አለብን ያሉት ጫማ ሰሪው ሪቻርድ ክዋርቴንግና ወንድሙ ጁድ ኦሴይ በፀሐይ ብርሃን የሚሰራ የእጅ መታጠቢያ ዲዛይን አድርገው ሰርተዋል።
ማሽኑ እጅ ቀረብ ሲል እንቅስቃሴን የሚረዳ ሲሆን ሳሙናና ውሃም ወዲያውኑ ይለቃል። ከሃያ አምስት ሰኮንዶች በኋላ የደወል ድምፅ ያሰማና ያቆማል። የዓለም ጤና ድርጅት ሃያ ሰኮንዶች እጅ መታጠብ ያስፈልጋል የሚለውንም መመሪያ ተግባራዊ ተደርጎበታል።
- የሳንባ ኤክስሬይን በማየት የኮሮናቫይረስ ሁኔታን ማወቅ የሚያስችለው መሳሪያ
በቱኒዝያ የሚገኙ መሃንዲሶች በበይነ መረብ አማካኝነት ሳንባን ኤክስሬይ ማድረግ ችለዋል። ውጤቱንም በማየት ግለሰቡ በኮሮናቫይረስ ተጠቅቷል ወይስ አልተጠቃም የሚለውንም ይወስናል።
በፈጠሩት ድረገፅ ላይ ኤክስሬዩ ሲጫን ምስሉን በማየት በኮሮናቫይረስ መጠቃት አለመጠቃቱን ይመረምራል ውጤቱንም ያሳውቃል።
በቱኒዝያ የሚገኘው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ብሔራዊ የምርምር ተቋምም መሳሪያው 90 በመቶ አስተማማኝነቱን የመሰከረ ሲሆን የሳንባውን ኤክስሬይ በመመርመር በኮሮናቫይረስ የመጠቃት ሁኔታቸውን ማወቅ ያስችላልም ብሏል።
ድረገፁ ሙሉ በሙሉ ያልተጠናቀቀ ቢሆንም በሺዎች የሚቆጠሩ የሳንባ ኤከስሬይ ውጤቶችንም ተሞክሮበታል።
- የሮቦት ፖሊሶች
የተለያዩ አገራት አስገዳጅ የቤት ውስጥ መቀመጥ መመሪያን ለማስከበር የተለያዩ እርምጃዎችን ወስደዋል። ቱኒዝያ ደግሞ በመዲናዋ ቱኒዝ ይህንን መመሪያ ለማስከበር የሮቦት ፖሊሶችን አሰማርታለች። ይህንንም በሚያዝያ ወር ላይ ነው ያስተዋወቀችው።
ፒጋርድስ የሚባል መጠሪያ የተሰጣቸው ሮቦቶች ወደ ጎዳናዎች የሚወጡ ቱኒዝያውያን ላይ ይሰልሉ ነበር። ቀረብ ብለውም ከቤታቸው ለምን እንደወጡ ይጠይቃሉ። ደንብ የጣሱ ግለሰቦችም መታወቂያና ሌሎች መረጃዎችን በሮቦቱ ለተገጠመው ካሜራ ማሳየት አለባቸው። ባለ አራት ጎማዎቹ ሮቦቶች ካሜራዎችን ጨምሮ፣ ብርሃን መለየትና ሌሎች ቴክኖሎጂም ተገጥሞላቸዋል።
- መገበያያ ገንዘቦችን የሚያፀዳው መሳሪያ
ኬንያዊው የተንቀሳቃሽ ስልኮች ገንዘብ ወኪል ዳንሰን ዋንጆሂ የመገበያያ ገንዘቦችን በፀረ-ተህዋሲያን የሚያፀዳ ከእንጨት የተሰራ ማሽን ሰርቷል። ማንኛውም ገንዘብ በማሽኑም እንዲያልፍ ይደረጋል።
ዳንሰን ይሄንን መሳሪያ ሞተር፣ የብር ፕላስቲክና ሌሎች በቀላሉ የሚገኙ ቁሳቁሶችን በመጠቀም ነው የገጣጠመው። ገንዘቡ በማሽኑ ውስጥ ሲያልፍም በፀረ ተህዋሲያን ይፀዳል።
- በ65 ደቂቃ ውጤት የሚያደርሰው ፈጣኑ የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ
የደቡብ አፍሪካ ቴክኖሎጂ ፈጣሪዎቹ ዳንኤል ንዲማና ዲኒዮ የኮሮናቫይረስን በፍጥነት መመርመር የሚያስችልና በ65 ደቂቃም ውጤትዎን ተቀብለው መሄድ የሚችሉበትን መሳሪያ ፈልስፈዋል።
በተለመደው አሰራር ከሆነ ተመርምረው ውጤት ለማግኘት ሦስት ቀን ይወስዳል። የመመርመሪያው መሳሪያ ኪው ሲፒ አር የሚባል ስያሜ ያለው ሲሆን ዲኤንኤን መመለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂም ተገጥሞለታል። መሳሪያው ተግባር ላይ ከመዋሉ በፊት ውጤታማነቱ በተቆጣጣሪ አካል ተገምግሞ እውቅና ሊሰጠው ይገባል።
- አካላዊ ርቀት ያለበት የፀጉር አስተካካዮች
በኢትዮጵያ የሚገኙ የፀጉር አስተካካዮች ደንበኞቻቸው ለኮሮናቫይረስ እንዳይጋለጡ በማሰብ አካላዊ ርቀትን የጠበቀ መላን ዘይደዋል።
ፀጉር አስተካካዮቹ በሌላ ክፍል ሆነው ደንበኛው ውጭ ሆኖ ወንበር ላይ ይቀመጣል። በመስኮት በኩል ሆኖም እጁን ብቻ በማውጣት ፀጉር ያስተካክላል።
ይህም የቅርብ አካላዊ ንክኪንና የትንፋሽ ልውውጥን ለመቀነስ ታስቦ ነው።