ኮሮናቫይረስ፡ አፍሪካ ከገባ ግማሽ ዓመት የሞላው ወረርሽኝ ወዴት እያመራ ነው?

አህጉረ አፍሪካ የመጀመሪያው ሰው በኮሮናቫይረስ ተይዞብኛል ብላ ካወጀች እነሆ ግማሽ ዓመት ሆነ።

አህጉሪቱ ውስጥ የመጀመሪያ በቫይረሱ የተያዘ ሰው ይፋ የተደረገው ግብፅ ውስጥ ነው። ይህ ዜና ከተሰማ በኋላም ቢሆን ወረርሽኙ አፍሪካ ላይ ብርቱ ክርኑን ወዲያው አላሰረፈም ነበር።

አውሮፓውያን እንደቅጠል ሲረግፉ፤ አሜሪካውያን ለሞት ሲሰለፉ፤ አፍሪካ ግን ሃገር ሰላም ብላ ነበር። ይህ ለምን ሆነ ብለው የተንገበገቡ ሰዎች ጥናት እናካሂድም ብለው ነበር።

ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአህጉሪቱ ሃገራት በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ነው።

በቀን አንድና ሁለት ሰው የመዘገበችው ኢትዮጵያ እንኳ ትላንት [ነሐሴ 8/2012] በ24 ሰዓታት ብቻ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ይፋ አድርጋለች።

ደቡብ አፍሪካ በበኩሏ ከአህጉር አልፋ በዓለም ደረጃ መወዳደር ይዛለች። በአሁናዊ አሃዝ መሠረት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮሮናቨይረስ የተያዙባት ደቡብ አፍሪካ በዓለም አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ከደቡብ አፍሪካ በተጨማሪ ግብፅ፣ ናይጄሪያ፣ ጋና እና አልጄሪያ፤ በአፍሪካ በኮሮናቫይረስ ከተያዙ ሰዎች 75 በመቶ ገደማ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛሉ።

ምንም እንኳ ቁጥሩ ከጊዜ ጊዜ ቢጨምርም የዓለም ጤና ድርጅት ወረርሽኙ አፍሪካ ላይ መች እንደሚበረታ መገመት አልቻልኩም እያለ ነው።

ድርጅቱ የአፍሪካ ሃገራት የኮሮናቫይረስ ምርመራቸውን በገጠራማ ሥፍራዎችም እንዲያከናወኑ በፅኑ ያሳስባል። በተለይ ደግሞ ድንበር አካባቢ ያሉ ከተማዎች የቫይረሱን ሥርጭት መጠን የሚያሳዩ ናቸው ይላል ድርጅቱ።

አውሮፓና አሜሪካ በወረርሽኙ ሲደናገጡ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥለው የነበሩ የአፍሪካ ሃገራት አሁን ወረርሽኙ ፊቱን ወደ አህጉሪቱ ቢያዞርም እንቅስቃሴዎችን ማላላት ጀምረዋል።

ከ54ቱ የአህጉሪቱ ሃገራት 25ቱ ድንበራቸውን ዘግተዋል። 23 ደግሞ ወደ ሃገር ለሚገቡና ለሚወጡ ሰዎች የግዴታ የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንዲያከናውኑና የምርመራ ውጤት እንዲያመጡ ያዛሉ።

የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠር ማዕከል [ሲዲሲ] በላይቤሪያ፣ ሲዬራ ሊዮን፣ ዛምቢያ፣ ዚምባብዌ፣ ካሜሩንና ናይጄሪያ ውስጥ የበሽታ መከላከል [አንቲቦዲ] ምርመራ ላከናውን ነው ብሏል። ማዕከሉ ይህን ማድረግ ያስፈለገው በሽታው በምን ያክል ፍጥነት እየተጓዘ እንዳለ ለመረዳት ነው።

የአንቲቦዲ ምርመራ ማለት ሰዎች ከዚህ በፊት በኮሮናቫይረስ ይሆን ወይ የሚለውን የሚለይ ነው።