በደቡብ አፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ከግማሽ ሚሊዮን አለፈ

በደቡብ አፍሪካ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን የአገሪቷ የጤና ሚኒስትር አስታወቁ።

የጤና ሚኒስትሯ ዚዌሊኒ ምክሂዝ እንዳሉት በአገሪቷ ቅዳሜ ዕለት ብቻ 10 ሺህ 107 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ አጠቃላይ ቁጥሩን 503 ሺህ 290 አድርሶታል።

እስካሁን 8 ሺህ 153 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ አህጉር ከሚገኙ አገራት ክፉኛ በቫይረሱ የተጎዳች ሲሆን በአገሪቷ የተመዘገበው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም በአህጉሩ ከተመዘገበው ግማሽ ያህሉን ነው ተብሏል።

አገሪቷ በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ቁጥርም አሜሪካ ፣ ብራዚል፣ ሩሲያና ሕንድን ተከትላ በአለም አቀፉም በአምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። በአገሪቷ ያለው የሟቾች ቁጥርም ይፋ ከተደረገው የላቀ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የደቡብ አፍሪካ የጤና ባለሥልጣናት በፕሪቶሪያ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ጠቅሰው የወረርሽኙ ሥርጭት በፍጥነት እየተስፋፋ እንደሆነ አስጠንቅቀዋል።

ከአጠቃላይ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሦስተኛ የሚበልጠው በአገሪቷ የንግድ ማዕከል ጋውተንግ የተመዘገበ ሲሆን ሌሎች ግዛቶችም የወረርሽኙ ማዕከል ሆነዋል ብለዋል።

ደቡብ አፍሪካ የወረርሽኙን ሥርጭት ለመግታት በሚያዝያና ግንቦት ወር ላይ ጥብቅ የሆነ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላ ነበር።

እነዚህ ገደቦች ሰኔ ወር ላይ ቀስ በቀስ መላላት የጀመሩ ቢሆንም የወረርሽኙ ስርጭት እንደገና መስፋፋቱን ተከትሎ የአልኮል ሽያጭን ጨምሮ ሌሎች ገደቦች ደግሞ ባለፈው ወር ጀምሮ እንደገና ተጥለዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ለመጭዎቹ 15 ቀናት በሥራ ላይ እንደሚቆይ ተነግሯል።

በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር በሆስፒታሎች ላይ መጨናነቅ የፈጠረ ሲሆን የጤና ባለሙያዎች መዳከማቸውንና የጤና አገልግሎቱም እጅግ የተዳከመ መሆኑን ቢቢሲ በምርመራው አረጋግጧል።

ባለፈው ወር ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ለኮቪድ -19 ታማሚዎች 28 ሺህ የሆስፒታል አልጋዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረው፤ ነገር ግን ከፍተኛ የሆነ የዶክተሮችና ነርሶች እጥረት እንዳለባቸው ተናግረው ነበር።

ባለፈው ሳምንትም የዓለም ጤና ድርጅት የደቡብ አፍሪካ ልምድ በአህጉሯ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አመላካች ነው ሲል ማስጠንቀቁ ይታወሳል።