አሜሪካ፡ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ታናሽ ወንድም ሞቱ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ "የልብ ወዳጄ" የሚሉት ታናሽ ወንድማቸው ህይወቱ በማለፉ የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል።

"በተሰበረ ልብ ነው የምወደው ወንድሜ ሮበርት ዛሬ ምሽት ህይወቱ ማለፉን የምናገረው" በማለት በትናንትናው ዕለት ባወጡት መግለጫ አስፍረዋል።

የ71 አመቱ ሮበርት በኒውዮርክ ሆስፒታል ውስጥ በነበሩበት ወቅትም ፕሬዚዳንቱ የጎበኟቸው ሲሆን ለጋዜጠኞችም "ፈታኝ ጊዜ ላይ ነው ያለው" ብለው ነበር።

ሮበርት ትራምፕ የሞቱበት ምክንያት አልተገለፀም።

በርካታ የአገሪቱ ሚዲያዎች በጠና ታመው እንደነበር ዘግበዋል።

"ወንድሜ ብቻ አልነበረም፤ ሁሉን ነገር የማዋየው የልብ ጓደኛዬ ነበር" ፕሬዚዳንቱ ማለታቸውን የትናንትናው መግለጫ አስነብቧል።

"ጥሎልልን ያለፈው ትዝታው ሁሌም አብሮን ይኖራል" ብለዋል።

የፕሬዚዳንት ትራምፕ ልጅ ኤሪክ አጎቱን "ድንቅ፣ ጠንካራ፣ ቀና፣ ሩህሩህና በጣም ታማኝ ሰው ነበር" ሲል ገልጿቸዋል።

አክሎም ቤተሰቡ ሁሉ እንደሚናፍቃቸው በትዊተር ገፁ አስፍሯል።

ሮበርት ከፕሬዚዳንቱ በሁለት አመት የሚያንሱ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን፤ በአጠቃላይ የቤተሰቦቹም ልጆች አምስት ናቸው።

ሮበርት ትራምፕ ሙሉ የስራ ዘመናቸውን የቤተሰቡን የቤቶች ግንባታ ኢንዱስትሪ በበላይነት ሲቆጣጠሩ የነበረ ሲሆን እስከ እለተ ሞታቸው ድረስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ነበሩ።

ከወንድማቸው ዶናልድ ትራምፕ በተለየ መልኩ የሚዲያ አትኩሮትና ዝናን የማይወዱ፣ ኑሯቸውንም በኒውዮርክ ገለል ባለ ስፍራ የነበረ ነበር።

በቅርቡም የወንድማቸው ልጅ ሜሪ ትራምፕ ስለ ትራምፕ "ቤተሰባችን አደገኛ ሰው እንዴት ፈጠረ" የሚል የፕሬዚዳንቱን ጉድ የሚዘከዝክ መፅሃፍ ከማሳተም ለማስቆምም ፍርድ ቤት ሄደው ነበር።

ኒውዮርክ ፖስት ባሳተመው ፅሁፍ ሮበርት በማንሃተን በሚገኘው ሲናይ ሆስፒታል ከሳምንት በላይም በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ነበሩ ብሏል።