ሩብ ሚሊዮን ዩሮ ከአገር ሊሸሽ ሲል ያጋለጠው ውሻ

አንድ ስልጡን ውሻ የጀርመን ባለሥልጣናት እየተወደሰ ነው፡፡ ከሰሞኑ ወደ 250ሺሀ ዩሮ ከአገር ሊሸሽ ሲል በፍራንክፈርት አየር ጣቢያ እንዲያዝ አድርጓል፡፡

ይህ ጀብድ የመጀመርያው አይደለም፡፡

አኪ የተባለው ይህ አነፍናፊ ስልጡን ውሻ ከሰኔ እስከ ሐምሌ ባለው ጊዜ ብቻ 12 ሰዎች ብር ከአገር ሊያሸሹ ሲሉ አጋልጧቸዋል፡፡

በአንድ አጋጣሚ ለምሳሌ 52ሺህ ዩሮ በኪሱ አጭቆ ከአገር ሊወጣ የነበረውን ሰው ይኸው ውሻ አንጠልጥሎ ከአውሮፕላን አውጥቶታል፡፡

ተጓዦች ከአውሮጳ ኅብረት ክልል ውጭ እንዲህ ከፍ ያለ ገንዘብ ፍቃድ ሳያገኙ ይዘው እንዲወጡ አይፈቀድላቸውም፡፡

በአውሮፓ ኅብረት የገንዘብ ዝውውር መመሪያ መሠረት ወደ ሦስተኛ አገራት የሚጓዝ መንገደኛ ከ10ሺህ ዩሮ በላይ በካሽ በኪሱ ይዞ መውጣት አይችልም፡፡ ከ10ሺ ዶላር በላይ ይዞ መውጣት ብቻ ሳይሆን ይዞ የሚገባ ተጓዥም ገንዘቡን ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡

አኪ የተባለው አነፍናፊው ሥልጡን ውሻ የጉምሩክ ፖሊሶች ሊደርሱበት ያልቻሉትን ገንዘብ እስተላላፊ ተጓዥ ያለምንም ጥርጥር ለይቶ ይዞታል፡፡

አኪ ውሻ የያዛቸው ረብጣ ዶላሮችና ዩሮዎች በሱሪ ኪስ፣ በእጅ ቦርሳ፣ በጀርባ በሚታዘል ቦርሳ እና በጃኬት ውስጥ የታጨቁ ነበሩ፡፡

‹‹ገንዘብ አይከረፋም›› የሚለውን የእንግሊዝኛ አባባል አፈር ድሜ አብልቶታል ስልጡኑ አኪ ውሻ ብለዋል ኢሳቤል ጊልማን፡፡ ኢሳቤል ጊልማን በፍራንክፈርት አየር ማረፊያ የጉምሩክ ባለሥልጣን ቃል አቀባይ ናቸው፡፡

አኪ በሚል የሚቆላመጠው ይህ ስልጡን አነፍናፊ ወሻ 9 ዓመቱ ነው፡፡

በዚህ ዘመን ስልጡን አነፍናፊ ውሻዎች ካንሰርና ስኳር ያለባቸውን ሰዎች እንዲለዩ እየሰለጠኑ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የኮቪድ-19 ያጠቃውን ሰው ነጥለው ማውጣት እንዲችሉ ስልጠና እያገኙ ነው፡፡

ይህም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይሳካል ተብሎ ይጠበቃል፡፡