ውሻ ይዛ መስጅድ የገባችው ሴት ምህረት ተደረገላት

ውሻ ይዛ መስጅድ የገባችው ኢንዶኔዢያዊት አእምሮ ህመምተኛ ሴት ሃይማኖትን በመዳፈር ሊፈረድባት ከሚችለው እስር ምህረት ተደረገላት።

ሱዜት ማርጋሬት የተባለችው ሴት ጫማዋን ሳታወልቅ እና ውሻዋን አስከትላ ወደ መስጅድ ስትገባ የሚያሳያው ተንቀሳቃሽ ምስል በርካታ ኢንዶኔዢያዊያን ተጋርተውታል።

የማርጋሬት ተግባር በርካታ የዕምነቱን ተከታዮች አበሳጭቷል።

ውሾች በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በስፋት ንጹህ እንዳልሆኑ ይታመናል።

በማርጋሬት ላይ የቀረበውን ክስ መርምረው የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት የተሰየሙት ዳኞች፤ ተከሳሿ የአእምሮ ጤና መቃወያስ ያጋጠማት በመሆኗ ሃይማኖትን በመዳፈር በሚል ብይን መስጠት አንችልም ሲሉ በነጻ አሰናብተዋታል።

በርካቶች በተጋሩት ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ፤ ማርጋሬት የካቶሊክ ዕምነት ተከታይ መሆኗን በመጥቀስ ጫማዋን ሳታወልቅ ውሻዋን አስከትላ ወደ መስጅዱ ከገባች በኋላ፤ ባለቤቷ በመስጅዱ የሰርግ ስርዓቱን ለማከናወን ቀጠሮ መያዙን በብስጭት መናገር ትጀምራለች።

ማርጋሬት ባለቤቷ እምቱን ወደ እስልምና ለመቀየሩ መስጅዱን ተጠያቂ ያደረገች ሲሆን፤ መስጅዱን ለቃ እንድትወጣ የሞከረን ጥበቃ ለመማታትም ሞክራለች።

የመስጅዱ መሪዎች ማርጋሬት ስለምትለው ግለሰብም ይሁን ስለተያዘ የሰርግ ቀጠሮ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

ማርጋሬት የተባለው ችግር ባይኖርባት ድርጊቷ ቢያንስ ስምንት ወራትን በእስር እንድታሳለፍ ያስችላት ነበር ተብሏል።