ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ፡ በዓመት 125 ሚሊዮን ዶላር የተከፈላቸው የአፕል ሥራ አስፈፃሚ ቲም ኩክ ቢሊየነር ሆኑ
አፕል የተሰኘው ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ቲም ኩክ የኩባንያቸው አክስዮን ዋጋ እየናረ በመምጣቱ የቢሊየነሮችን ክለብ ተቀላቅለዋል።
847 ሺህ 969 የኩባንያ አክሲዮኖች ባለቤት የሆኑት ኩክ ባለፈው ዓመት ብቻ 125 ሚሊዮን ዶላር [ወደ ብር ስናመጣው ወደ 4.4 ቢሊዮን ገደማ] ደመወዝ ተከፍሏቸዋል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን እየሾሩ ላሉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ባለቤቶች ፍርቱና ሆኗል።
ይህ የሆነው ሰዎች በወረርሽኙ ምክንያት ቤት መዋል መጀመራቸውና የሚፈልጉት ምርትና አገልግሎት በበይነ መረብ አማካይነት ማሰስ መጀመራቸው ነው።
ባለፈው ሳምንት የፌስቡክ ባለቤት የሆነው ማርክ ዛከርበርግ የግል ሃብቱ ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ መግባቱ ተሰምቶ ነበር።
የዛከርበርግ ፌስቡክ ብቻ ሳይሆን አፕል፣ አማዞንና ማይክሮሶፍት ከወረርሽኙ ካተረፉ መካከል ናቸው።
በዋናነት በአሜሪካ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን የሚያመርተው አፕል 2 ትሪሊየን ዋጋ የሚያወጣ የመጀመሪያ የዓለማችን ኩባንያ ሊሆን ተቃርቧል። ከሁለት ዓመታት በፊት 1 ትሪሊየን ዋጋ ያለው የመጀመሪያው የዓለማችን ኩባንያ መሆን መቻሉ አይዘነጋም።
ቲም ኩክ የአፕል ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተሾሙት የስቲቭ ጆብስን [የኩባንያው መስራች] ሞት ተከትሎ ከ9 ዓመታት በፊት ነበር።
ሰውዬው ሃብታቸው ቢሊዮን የደረሰው ከአክሲዮን ከሚያገኙት ገቢና ድርጅቱ ከሚከፍላቸው ደመወዝ ነው።
በጎርጎሳውያኑ 2015 አብዛኛውን ገንዘባቸውን ለእርዳታ ድርጅቶች እንደሚያበረክቱ ቃል የገቡት ቲም ቃላቸውን ሳያጥፉ በርካታ ሚሊዮን ዶላሮች ይለግሳሉ።
የፌስቡኩ ዛከርበርግም እንዲሁም ሚሊዮን ዶላሮችን ዝቄ ለእርዳታ ድርጅቶች እሰጣለሁ ሲል ቃል መግባቱ አይዘነጋም።
የፌስቡክ ፈጣሪው ዛከርበርግ፣ የአማዞን ባለቤት ጄፌ ቤዞስና የቴስላ መሥራች ኢላን ማስክ የግል ሃብታቸው በየቀኑ የሚያድገው በኩባንያዎች ውስጥ ባላቸው ትልቅ የአክሲዮን ድርሻ አማካይነት ነው።
ምንም እንኳ አፕል እንደፈጠረው ተንቀሳቃሽ ስልክ ያለ ገበያውን ያመሰ አዲስ ምርት ባይኖረውም ኩባንያው አሁንም ጥንካሬውን እያሳየ ነው።
ቲም ኩክ ኩባንያውን በኃላፊነት ከተረከቡት በኋላ የተለያየ ዓይነት የአይፎርን ምርቶች ለገበያ አቅርበዋል። አፕል ዎች የተሰኘ የተንቀሳቃሽ ስልክ ባህሪ ያለው የእጅ ሰዓትም ለገበያ አቅርበዋል።
ከሌሎቹ ጉምቱ ባለሃብቶች ሲነፃፀር የቲም ኩክ ሃብት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
በካሊፎርኒያ የግብር ሕግ መሠረት ቲም ኩክ 50 በመቶ ግብር እንዲከፍሉ ሊገደዱ ይችላሉ።