ኮሮናቫይረስ ፡ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ100 በላይ ሠራተኞች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተነገረ

በሲዳማ ክልል በሚገኘው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ ከ100 በላይ ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸውን የክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ማቴ መንገሻ ለቢቢሲ ገለፁ።
ክልሉ ባለፉት 12 ቀናት በኢንዱስትሪ መንደሩ ባደረገው ምርመራ የኢንዱስትሪ መንደሩ ሠራተኞች በኮሮናቫይረስ መያዛችን ያረጋገጠ ሲሆን፤ ቫይረሱ በተለይ በሁለት ማዕከላት (ሼዶች) ውስጥ ተስፋፍቶ እንደሚገኝ ዶ/ር ማቴ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በኢንደስትሪ ፓርኩ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱን ያረጋገጡት አንድ ሠራተኛ ከ12 ቀን በፊት ታሞ በፓርኩ በሚገኝ ክሊኒክ ለሕክምና በመሄዱና ምልክቶቹ የኮሮናቫይረስ መሆናቸው በመረጋገጡ ጥቆማ ደርሷቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ግለሰብ እንዲሁም ከባሕር ማዶ የመጡ የድርጅቱ ሠራተኛ ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች ሲመረመሩ ከ100 በላይ ሰዎች ተይዘው መገኘታቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።
እንደ ዶ/ር ማቴ ከሆነ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ንክኪ አላቸው ተብሎ ከሚታመኑ ሰዎች በአጠቃላይ ናሙና እየተወሰደ ነው።
ከፍተኛ ንክኪ አለው ተብሎ የተገመተው አንድ ሼድ ሲሆን ስምንት መቶ ያህል ሠራተኞች እንዳሉት ገልፀው፤ ሁሉንም ሠራተኞች ለመመርመር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዶ/ር ማቴ አክለውም ከሁለተኛው ሼድ ግን ሙሉ በሙሉ አለመወሰዱን ተናግረዋል።
በቫይረሱ ከተያዙት ሠራተኞች መካከል የውጭ አገር ዜጎች፣ የሰው ኃይል አስተዳደር ላይ የሚሰሩ ሠራተኞችና፣ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ግንኙነት የነበራቸው ኦፕሬተሮች መሆናቸውን ጨምረው ገልፀዋል።
እነዚህ በቫይረሱ ተይዘው የሚገኙት ሰዎች የኢንዱስትሪ ማዕከሉ ውስጥ ባሉ በሁለት ሼዶች ውስጥ ሚሰሩ እንደሆኑ ተናግረዋል።
"በኢንደስትሪ ፓርኩ ያለውን ስርጭት ተቆጣጥረናል ማለት ይቸግረና" ያሉት ዶ/ር ማቴ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ መግባታቸውንና ንክኪ ያላቸውን ለመለየት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ ኮሮናቫይረስ መከላከል ባለሙያዎች በኢንዱስትሪ ፓርኩ ያለውን ንክኪ ለመለየት፣ ግንዛቤ ለማስጨበጥና ትምህርት መስጠት ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።
ከዚህ በተሻለ ግን የቫይረሱን ስርጭት ባለበት ለማቆም ከኢንደስትሪ ፓርኩ ጋር በመነጋገር ቫይረረሱ በስፋት የታየበት ሼድ ለተወሰነ ገዜ ሥራ እንዲያቆምና ሠራተኞች ራሳቸውን ለይተው እንዲቀመጡ ለማድረግ ቢታሰብም ውጤታማ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
ዶ/ር ማቴ አክለውም እስከ ዛሬ ድረስ በሲዳማ ክልል 13 የሕክምና ባለሙያዎች እና ሁለት ድጋፍ ሰጭ ሠራተኞች በኮቪድ-19 መያዛቸውን ተናግረዋል።
በኮቪድ-19 ከተያዙት የሕክምና ባለሙያዎች መካከል ወደተለያየ ስፍራ ሄደው ራሳቸውን ለቫይረሱ ያጋለጡ፣ በሚሰሩባቸው ተቋማት አካባቢ ባለ የጥንቃቄ ጉድለት እንዲሁም የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት በመኖሩ የተነሳ የተጋለጡ እንደሚገኙበት አብራርተዋል።
የሲዳማ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዳይሬክተሩ በክልሉ እስካሁን ድረስ 452 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ገልፀው፤ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘም አምስት ሰዎች መሞታቸውን ገልፀዋል።
የሐዋሳ የሚገኘው ኢንዱስትሪያል ፓርክ በአገሪቱ ካሉ መሰል ተቋማት መካከል ከትልልቆቹ ጋር የሚመደብ ሲሆን በውስጡ የተለያዩ ምርቶችን የሚያመርቱ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማት ይገኙበታል።
ፓርኩ በአሁኑ ጊዜ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ያሉበት ሲሆን ከጥቂት ዓማት በፊት ተከፍቶ ሥራውን በጀመረበት ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ በውስጥ ያሉት ሁሉም ፋብሪካዎች ሥራ ሲጀምሩ ከ60 ሺህ በላይ ሠራተኞችን ይቀጥራል ተብሎ እምነት ተጥሎበት ነበር።

















